​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

ዕድሜያቸው ከ45ና ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች ማንበብ የሚገባቸው
አዲስ የአንጀት ካንሰር ቅድሚያ ምርመራ (screening) መመሪያ

06/27/2021


በወረርሽኙ ተወጥረን፣ ለረዥም ጊዜያት ለሰዎች ህይወት ህልፈት ምክንያት የሚሆኑ ሌሎች በሽታዎችና ካንሰሮች መኖራቸው የተዘናጋን ይመስላል፡፡ ሆኖም ባለሙያተኞቹ ጉዳዮችን በመከታተል አዳዲሰ መመሪያዎችን እያወጡ ነው፡፡

ለዚህ አዲስ የአንጀት ካንስር ቀድሚያ ምርመራ መለወጥ ምክንያት በ43 አመቱ ሕይወቱ ያለፈው የሲኒማ ተዋናይ ነው፡፡ ብላክ ፓንተር የሚባለውን ሲኒማ ያየ ሰው ኮከብ ተዋናዩን ያስታውሳል ብዬ እገምታለሁ፡፡

ተዋናዩ ቻድዊክ ቦስማን በ2016 አንጀት ካንሰር እንዳለበት ከታወቀ ጀምሮ የተለያዩ ህክምናዎችን ሲያደርግ ቢቆይም፣ ካንስሩ ተስፋፍቶ ደረጃ አራት በመድረስ ገና እያደገ ያለው ይህን ኮከብ ተዋናይ በ43 አመት ዕድሜው ሕይወቱ አልፏል፡፡ የሱ ሞት የሙያ ባልደረቦችን ማሰደንገጡ ብቻ ሳይሆን በህክምናው አለም ደግሞ በተለይም በካንሰሩ በኩል፣ ሀኪሞችንም ያስደነገጠ ነገር ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አንጀት ካንሰርን በተመለከተ ከዚህ በፊት የነበረውን መመሪያ እንደገና መመርመር አስፈላጊ ነበር፡፡ መመሪያዎች ሲወጡም ሆነ ሲቀየሩ የተለያዩ መረጃዎቸን በመመርኮዝ ነው፡፡

ወደ አዲስ ቀድሞ ምርመራ መመሪያ ከመሄዳችን በፊት፣ ሰለ አንጀት ካንሰር መጠነኛ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ለምንስ ይህ ካንሰር ትልቅ አትኩሮት ተሠጠው ማለትም ተገቢ ነው፡፡

በ2018 በቀረበ መረጃ የአንጀትና የሠገራ መውጫ ካንሰር (Colorectal cancer, CRC)፣ በአለም አቀፍ ደረጃ በካንሰር ምክንያት የሰዎች ህይወትን በመቅጠፍ ሶሰተኛውን ደረጃ የያዘ ሲሆን፣ በአለም አቀፍ ደረጃም በምርመራ ከሚታወቁ ካንሰሮች በአራተኛ ደረጃ ይገኛል፡፡ ከሁሉም ካንሰሮች 11 ፐርሰንቱን ይይዛል፡፡ የሚያሳዝነው ይህ ካንሰር (CRC) ያለማቋረጥ ቁጥሩ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ሌላው አሳሳቢ ችግር፣ ይህ ካንሰር በታዳጊ አገራት ላይ በመጠን እየጨመረ መሄዱ ይታወቃል፡፡ ይህንን በታዳጊ አገራት የካንሰሩ መጠን መጨመር፣ አገራቱ የምዕራባውያንን የአኗኗር ሁኔታ በመከተላቸውም ነው ይላሉ፡፡

የምዕራባውያን የአኗኗር ሁኔታ ምንድን ነው ከማለታችሁ በፊት፣ ልጨመር፡፡ እነዚህ ባህሪዎች ከመጠን በላይ ውፍረት፣ የሰውነት አንቅስቃሴ መቀነስ፣ ቀይ ሥጋ ማዘውተር፣ አልኮል ማዘውተርና ሲጋራ ማጨስ የካንሰሩ መጠን እንዲጨምር የሚያደርጉ ሀኔታዎች ናቸው፡፡

የካንሰሩ መጠን እየጨመረ ቢሄድም፣ አስቀድሞ ምርመራ በማድረግ ካንሰሩ ከመስፋፋቱ በፊት በጊዜ ማወቅና ተከትሎም በሚደረግ ህክምናና ክትትሎች ምክንያት በዚህ ካንሰር ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን ሞት መጠን እንደቀነሰውም ይታወቃል፡፡ አነዚህ አስቀድሞ ምረመራ ማድረጊያ ዘዴዎችም እየተሻሻሉ መምጣታቸው ደግሞ ሌላው ጠቃሚ ነገር ነው፡፡

ወደ ችግሩ ስፋት ስንመለስ፤ በ2018 ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ በሆኑ ሰዎች በአንጀት ካንሰር መያዛቸው በመርመራ ሊገኝ ይችላል፡፡ የሠገራ መውጫ የሚታየው ካንሠር ሲጨመር፣ በ CRC የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 1.8 ሚሊዮን ከፍ ይላል፡፡ ይህ አሃዝ እንግዲህ በየአመቱ የሚከሰት ነው፡፡ አሁንም ወደ መመሪያው ከመሻገሬ በፊት አንዳንድ ነጥቦችን በመጨመር ለምን ትኩረት መሥጠት አሰፈላጊ መሆኑን አንድ ላይ እንገንዘብ፡፡ ይህ የአንጀትና የሠገራ መውጫ ካንሰር ከሴቶች በላይ በወንዶች ላይ በብዛት ይታያል፡፡ በተዳጊና ባደጉ አገሮች መሀከል ሲነፃፀር ባደጉ አገሮች ከሶስት እሰከ አራት ዕጥፍ ባደጉ አገሮች ላይ ይታያል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን የአኗኗር ሁኔታ ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡ [i]

ለማነፃፀር የዚህ ካንሰር ግኝት ከመቶ ሺ ሰዎች ምን ያህል በሚል ስሌት ሲገለፅ፤

በአለም አቀፍ ደረጃ ግኝቱ ከመቶ ሺ 19.7
በወንዶች                               23.6
በሴቶች                                16.3

ይህ ስሌት በአካባቢም ቢሆን ይገለፃል፣ የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ስንመለከት፣ የካንስሩ መጠን ከመቶ ሺ 7.7 ሲሆን በዚሁ ካንሰር ምክንያት የሞት መጠን ደግሞ 5.7 ነው፡፡ ይህ ሲጠቀስ ግን በቂ ምርመራ መደረግ መቻሉን፣ ምንስ ያህሉ ወደ ህክምና ቦታ ገብተው ተቆጥረዋል ብሎ ማስተዋል ያሰፈልጋል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የሚገኙት አውስትራሊያና ኒውዚላንድ የካንሰሩ የመገኘት መጥን ከመቶ ሺ 36.7 ሲሆን፣ የሞት መጠን ደግሞ 11.1 ነው፡፡ በሰሜን አሜሪካ የካንሰሩ ግኝት መጠን 26.2 ሲሆን በዚህ ምክንያት የሚከሰተው የሞት መጠን 8.4 ነው፡፡

ባጠቃላይ ሲታይ የአንጀትና የሠገራ መውጫ ካንሰር ተደርቦ በአለም አቀፍ ደረጃ በካንሰር ምክንያት የሰዎቸን ሞት በማስከተል ሁለተኛ ደረጃ የያዘ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን መጠነኛ መረጃዎች ከተመለከትን ይህ ካንሰር ምን ያህል አደገኛ መሆኑን መረዳት እንችላለን፡፡

ወደ አሜሪካ ስንመለስ በካንሰር ጉዳይ አሰቀድሞ ምርመራ የማድረግ መመሪያዎችን የሚያወጣው የአሜሪካ ካንሰር ሶሳይቲ (American Cancer Society) የሚባል ድርጅት ነው፡፡ ቀዳሚ ባለጉዳይም ይህ ድርጅት ነው፡፡

ድርጅቱ በቅርቡ ባወጣው አዲስ ሳይሆን በተሻሻለው መመሪያ ለአንጀትና የሠገራ መውጫ ካንሰር ቅድሚያ ምርመራ (Screening) ከዚህ በፊት ከሀምሳ አመት ይጀመር የነበረው በዕድሜ ዝቅ ብሎ በ45 አመት እንዲጀመር ይመክራል፡፡ ቅድሚያ ምርመራ ሲደረግ ሰዎች በተለያዩ ደረጃዎች ይመደባሉ፡፡

የመጀመሪያው በአንግሊዘኛ Average Risk የሚመደቡ ማለትም ለዚህ ካንሰር መከሰት ሰበብ ወይም ምክንያት የሌለባቸው ናቸው፡፡ ቅድሚያ ምርመራው ከአርባ አምስት አመት ጅምሮ አስከ 75 አመት ዕድሜ ድረስ እንዲቀጥል ነው የሚመከረው፡፡ ከሰባ ስድስት አመት አስከ ሰማንያ አምስት አመት ዕድሜ ክልል ላሉ ሰዎች፣ ቅድም ምርመራውን ለማድረግ የተመርማሪው ፍላጎት፣ የተመርማሪው የዕድሜ ጣሪያና አጠቃላይ የተመርማሪው ጤንነትና ከዚህ በፊት ይህንን ካንሰር በሚመለከት ከዚህ ቀደም ያደረጓቸው ምርመራዎችና ውጤት መታየት አለባቸው፡፡ ከ86 አመት ዕድሜ በላይ ለሆኑ ሰዎች ግን ይህን ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ አይደለም፡፡

ምን አይነት የቅድመ ምርመራዎቸ አሉ

ቅድመ ምረመራ ዘዴዎቹ በሁለት ይከፈላሉ፡፡ አንደኛው በሠገራ ምርመራ በኩል ሲሆን ሌላው ዘዴ ደግሞ በቀጥታ በመቀመጫ በኩል ገብቶ ትልቁ አንጀትን መመልከት የሚያስችል ቀጥታ ምርመራ ነው፡፡

  • Average Risk የሚመደቡ ሰዎች የሚከተሉት ሁኔታዎች የሌለባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ አበዛኛውን ሰው የሚያካትተው ምድብ ነው፡፡
  • አንደኛ ከዚህ ቀደም ይህ ካንሰር ያልታየባቸው ወይም በትልቁ አንጀት ውስጥ የሚያድጉ አንዳንድ ፖሊፕ የሚባሉ የሌለባቸው
  • ሁለተኛ በቤተሰብ ውስጥ ይህ ካንሰር ያልተገኘባቸው፡፡ ቤተሰብ ሲባል በሥጋ ዝምድና የሚገናኙ ለማለት ነው፡፡ ወላጆች፣ ወንድምና አህት፣ አጎት አክስትን የሚጨምር ነው፡፡
  • ሶሰተኛ ተመርማሪው አልሰሬቲቭ ኮላይቲስ ወይም ክሮንስ ዲዚዝ (Ulcerative Colitis or Crohn’s disease)የሚባሉ የአንጀት በሽታዎች የሌላቸው
  • አራተኛ የተረጋገጠ ወይም የሚጠረጠር በዘር አማካኝነት የሚመጡ የአንጀትና የሠገራ መውጫ ካንሰር ሊያስከትሉ የሚችሉ በሽታዎች የሌለባቸው ሰዎች
  •  አምሰተኛ ከዚህ ቀደም ለሌላ ካንሰር በተለይም በሆድ ዕቃና አካባቢው ላይ የጨረር ህክምና ያልተሠጣቸው ሰዎች


ከላይ የተዘረዘሩት ሁኔታዎች ለአንጀትና የሠገራ መውጫ ካንሰር ምክንያት ሰለሚሆኑና እነዚህ ሰዎች አደጋው ከፍ ሰለሚልባቸው በተለየ መልክ ምርመራና ክትትል ስለሚያሰፈልጋቸው ነው፡፡

የምርመራ ዘዴዎችን ስንመለከት

በአገልግሎት ላይ ያሉ የሠገራ ወይም የአይነ ምድር ምርመራ አጠቃቀም

  1. Highly sensitive fecal immunochemical test (FIT) በየአመቱ
  2. Highly sensitive guaiac-based fecal occult blood test (gFOBT) በየአመቱ
  3. Multi-targeted stool DNA test (mt-sDNA) በየሶሰት አመቱ


እነዚህ ምርመራዎች፣ ተመርማሪው በሚሰጠው የአይነ ምድር ናሙና ላይ የሚደረጉ ሰለሆነ፣ ተመርማሪው የሚያደርገው አይነ ምድር መስጠት ብቻ ነው፡፡

ሌላው ምርመራ ደግሞ በቀጥታ ካሜራ በተጠመደበት መሣሪያ በመቀመጫ በኩል በመግባት የሚደረግ ምርመራ ሲሆን፡፡ መርማሪ ሀኪሙ በአይኑ ማየት መቻሉና፣ ያየውንም ነገር እዛው ላይ ቅንጣቢ ናሙና በመውሰድ ለሌላ ተጨማሪ ምርመራ መላክ መቻሉ ከፍተኛ ጠቀሚታ አለው፡፡ ሆኖም ይህን ምርመራ ለማድረግ ተመርማሪው ወደ የአንጀት ህክምና ስፔሻሊሰት ተልከው፣ ከምርመራው በፊት ደገም አንጀት ከአይነ ምድር እንዲፀዳና ንፁህ ዕይታ እንዲኖር ተመርማሪው የታዘዘውን ፈሳሽ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ሙሉ ትልቁ አንጀት የሚታይበት ዘዴ ኮሎኖስኮፒ ይበላል፡፡

  1. ኮሎኖስኮፒ Colonoscopy ከሆነ በየአስር አመቱ ነው የሚደረገው
  2. ሌላው ደግሞ ሲቲ ስካን በሚባል ምርመራ ተደግፎ የሚደረግ ምርመራ CT colonography (virtual colonoscopy) ከሆኑ በየአምስት አመቱ
  3. እንደ ኮሎኖሰኮፒው ሙሉ በሙሉ ሳይሆን አስከተወሰነ የአንጀት ክፍል ድረስ ምርመራ የሚደረግበት Flexible sigmoidoscopy (FSIG) ከሆነ በየአምስት አመቱ ነው፡፡


ዕድሜዎ 45 አመት ከሞላ፣ ሀኪምዎን በመጠየቅ ይህ ምርመራ እንዲደረግሎው ማስደረግ በጣም ወሳኝ ነው፡፡

በነገራችን ላይ በሠገራ ወይም በአይነ ምድር ምርመራው ውጤት ላይ ካንሰር ሊኖር ይችላላ የሚባል ጥቆማ ካለ፣ ተመርማሪው ወደ ሰፔያሸሊሰቶች ተልኮ Colonoscopy እንዲያደርግ ይደረጋል፡፡ አሁን በተገኘው ውጤት አማካኝነት ሰለሆነ፣ ምርመራው የግድ ነው የሚሆነው፡፡

መመሪያው የአንጀትና የኮሎን ካንሰር ሊከሰትባቸው የሚችሉ አደጋ ላይ ላሉ ሰዎችም የሠጠው ምክረ ሀሳብ አለ፡፡ ነገር ግን ያ በራሱ ለየት ያለ አቀራረብ ሰለሚኖረው በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ማስገባት ተገቢ አይሆንም፡፡ ከዚህ በተያያዘ የምሠጠው ምክር ቢኖር፣ በቤተሰብ ወይም በዘር ሊከሰቱ ከሚችሉ በሽታዎች አንዱ ይህ ካንሰር ሰለሆኑ፣ እንድ የቤተሰብ አባል ላይ ከተከሰተ፣ ከላይ እንደጠቀስኩት በሥጋ ዝምድና በኩል፣ ሌሎች የቤተሰብ አባላት ሀኪሞቻቸውን ማማከር አለባቸው፡፡ እንደዚህ ሲሆን፣ ከአይነ ምድሩ ምርመራ ይልቅ ኮሎኖሰኮፒውን አድርጎ መገላገል ነው የሚሻለው፡፡ ሰለዚህ ካንሰር የተገኘበት የቤተሰብ አባልም ቢሆን፣ ሥራዬ ብሎ ሌሎቹን የቤተሰብ አባላት ማስታወቅ የሚመከር ነገር ነው፡፡

ይህን ፅሁፍ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ማካፈል ጥሩ ነው፡፡ ሰለዚህ የበኩልዎን ያድርጉ

ሌላ ፅሁፍ ሲወጣ ማወቅ ከፈለጉ በድረ ገፁ በሚገኘው ፎርም ኢሜል አደራሻ ብቻ በማስገባት ይመዝገቡ፡፡ ሌሎቹ ሳብስክራይብ እንደሚሉት ነው፡፡ ምዝገባው ፅሁፍ መውጣቱን እንዲያውቁ በኢሜል አደራሻዎ መልክት ለመላክ ነው፡፡

 
[i] Global cancer observatory