​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

​የስኳር በሽታ ጠንቅ የሆኑ የምግብ አይነቶች

በቅርቡ ሜዮ ክሊኒክ ፕሮሲዲንግ በተባለ መፅሔት ስለ ስኳር በሽታ ጠንቅ የሆኑ የምግብ አይነቶች በተለይም የስኳር አይነቶች ሰፋ ያለ ፅሁፍ ቀርቧል፡፡ ከዚህ ፅሁፍ አብይ የሆነውን ነገር ለማካፍል እንወዳለን፡፡ የስኳር በሽታ ሁለት አይነት ሲሆን ሁለተኛው አይነት በተለይ  በአዋቂ እድሜ የሚነሳ ሲሆን በአብዛኛው ከመጠን በላይ የሰውነት ክብደት መጨመርና በዘርም በቤተሰብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሀገር ቤት ወይም እዚህ በሚኖሩ ወገኖች ሁለተኛው አይነት የስኳር በሽታ በሚከሰትበት ጊዜ አብዛኞቹ ላይ ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት አለመታየቱ የሚያነጋግር ነገር ነው፡፡ ሰለዚሀ ከምግብ አይነትስ ጠንቅ ወይም ሰበብ ይኖር ይሆን ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ እንደ መፅሄቱ ዘገባ በእርግጥ የምንመገባቸው ነገሮች ለስኳር በሽታ መንስኤ እንደሚሆኑ ነው፡፡

ምግብ ላይ ስናተኩር በተለይ የስኳር አመጋገብን እንመለከታለን፡፡ ስኳር የተለያየ አይነት እንዳለውም መገንዘብ ይኖብናል፡፡ ስኳር ከመጠን በላይ መጠቀም ለተለያዩ የተዛቡ ሜታቦሊክ ( Metabolic syndrome) ክስተቶች እንደሚዳርግ ይታወቃል፡፡ በአንድ ጥናት  ወጣቶች የስኳር አጠቃቀማቸው በሁለት አይነተ ተከፍሎ ክትትል ከተደረገ በኋላ በአንዱ ወገን ከፍተኛ የስኳር መጠን በቀን 260 ግራም  የሚወስዱ በሌላው ወገን ደግሞ መጠነኛ ማለትም በቀን 115 ግራም ስኳር የሚወስዱ ሆነው የክትትል ውጤቱ ሲታይ ከፍተኛ የስኳር መጠን የሚወስዱት ላይ የኮለስትሮል መዛባት  እና ለኩላሊት በሽታ ቀዳሚ ምልክት የሆነ ኮምፓውንድ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ይህ ልዪነት የታየው በሶሰት ሳምንት ውስጥ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ከፍተኛ ስኳር የተመገቡት የስኳር መጠን እንዲቀንሱ ቢደረግም እሰከ ሁለት ሳምንት ድረስ ለጤና ጠንቅ የሆኑት ምልክቶች ወደ ጤናማ ደረጃ አልወረዱም፡፡

ወደ ስኳር አይነቶች ስንመለስ ሱክሮስ ና ፍሩክቶስ (Sucrose and Fructose) የሚባሉ ሲኖሩ በተለይ ፍሩክቶስ የተባለው የስኳር አይነት ለጤና ጠንቅ መሆኑ እየታወቀ ከመጣ ቆይቷል፡፡ የተለያዩ የምግብ አይነትና በተለይም መጠጦች ለማጣፈጫ በተጨማሪነት የሚዘጋጀው የስኳር አይነት ይህ ፍሩክቶስ በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ይህ የስኳር አይነት ለዳያቤትስ ወይም የስኳር በሽታ መከሰት በቀዳሚነት ደረጃ እንደሚገኝ ነው፡፡ ፍሩክቶስ በተፈጥሮ በሚገኝባቸው እንደፍራፍሬ አይነት ምግቦች ፍሩክቶስን ከመጥን በላይ ስለማይዙ ለምሳሌ እንደ ኮክ ፍሬ ፍሪዎችን መመገብ ችግር አያስከትልም፡፡ ሆኖም በፋብሪካ የሚመረቱ መጠጦች ተጨምቆ የተዘጋጀ ፍሩክቶስ ከመጠን በላይ ስለሚገኝባቸው እነዚህን መጠጦች በምንጠጣበት ጊዜ ለሰውነት ከሚገባው በላይ ፍሩክቶስ መጠቀማችን ነው፡፡ አነዚን በፋብሪካ የሚዘጋጁ መጠጦችን መጠቀም ጉልህ የሆነ የጤና ጠንቅ ይፈጠራል፡፡ ከተለያዩ ጥናቶች የተሰበሰበው ድህረ ጥናት መረጃ እንደሚያሳየው  ፍሩክቶስ ከሚገባው በላይ የሚገኝባቸው በፋብሪካ የሚመረቱ መጠጦችም ሆነ ምግቦችን መመገብ በደም ውስጥ ከጤናማ መጠን በላይ የሆነ የስኳር መጠን መታየት ጋራ የተያያዘ ነው፡፡  ይህንና ተጨማሪ መረጃዎችን በማካተት አጠር ባለ መልኩ የሚከተሉትን ነጥቦች ማሰተዋል ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ለአዋቂዎች ብቻ ሳይሆን ለሚያድጉ ወጣቶችም ሲባል መደመጥ የሚገባው ምክር ነው፡፡ ልጆችን በዘፈቀደ ከፋብሪካ የተመረቱ የምግብ አይነቶች መጠጦች ጭማቂዎችን ጨምሮ እንዲጠቀሙ ማድረግ ጠንቅ ማስከተሉን ማሰተዋል ተገቢ ነው፡፡

በምግብና በመጠጥ ላይ ስለሚጨመሩ ሰኳርና ፍሩክቶስ በሚመለከት ዋና ዋና ነጥቦች

በምግብ ላይ የሚጨመሩ ስኳርና ከፍተኛ ፍሩክቶስ ያለባቸው የበቆሎ ሲሮፕ (corn syrup) ለስኳር በሽታ ጠንቅ ናቸው ይህም የሰውነት ክብደት ከመጨመራቸው ጋራ ሳይያዝ ነው፡፡

ከፍተኛ ፍሩክቶስ ያለባቸው የበቆሎ ሲሮፕ (corn syrup) ለስኳር በሽታ መንስኤ ጠንቅነቱ ባጠቃላይ ተደምሮ ከሚወሰዱ የ ስኳር መጠኖችና ሌሎችም ምግቦች ከመጠን በላይ ባይሆኑም ነው፡፡ ማለትም ሲሮፑን መውሰድ ብቻ አደጋ እንዳለው ነው፡፡ 

የምግብ ዘይትና የስኳር በሽታ መከሰት ግንኙነት አላቸው፣ ጥናቶች ይጠቁማሉ

 
ሰለ ስኳር በሽታ ስንነጋገር ሁለት አይነት መኖራቸውን መገንዘብ አለብን፣ አይነት አንድና አይነት ሁለት ይሏቸዋል፡፡ (Type 1 and Type 2))፡፡ በዚህ ርዕስ የምንመለከተው አይነት ሁለት ሰለተባለው ነው፡፡ ይህም በአዋቂ ሰዎች ላይ የሚከሰት በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህ በአዋቂዎች ላይ የሚከሰተው አይነት ሁለት የስኳር በሸታ ሊከሰትባቸው የሚችሉ ሰዎች ተብሎ የተለያዩ ምክንያቶች ይዘረዘራሉ፡፡

  • ከመጠን በላይ ውፍረት

  • ዕድሜ 45 አመትን ከዛ በላይ

  • በቤተሰብ ውስጥ የስኳር በሽታ ካለ (በሥጋ ዝምድና) ወይ በዘር

  • የጥቁር ዝርያ

  • የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች

  • ሴቶች ከሆኑ ከርግዝና ጋር የተያያዘ የስኳር በሽታ ተከስቶባቸው ከሆነ

  • የሰውነት እንቅስቃሴ የማያዘወትሩ ከሆነ

  • በደም የኮለሰትሮል ምርመራ ላይ ጤናማው ኮለስትሮል (HDL) ዝቅተኛ ከሆነ ወይም ጮማ (Triglyceride) ከፍ ያለ ከሆነ

  • የልብ ህመም ኖሮት የሚያውቅ ከሆነ

  • አንገትዎ ወይም ብብትዎ አካባቢ ቆዳዎ ላይ ጠቆር ያለ እንደ ከፋይ የመሰለ ምልክት ካለዎት (በእንግለዝኛ Acanthosis Nigricans) ይባላል


ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ፣ በአብዛኛው የስኳር በሽታ የሚጀምራቸው ሰዎች፣ አብዛኞቹን አያሟሉም፡፡ እንዳውም ከሰውነት ውፍረት ይልቅ ቀጠን ያሉ ናቸው፡፡ በአብዛኛው፡፡ እናም፣ ሌላ ምክንያት ይኖር ይሆን፣ ከዚህ ጋር የተያያዘ የምግብ አይነት ይኖር የሚሆን የሚሉ ጥያቂዎች ደጋግመው ይነሳሉ፡፡ ከነዚህ መሀል፣ አንዱ ትኩረት የሠጠሁበት ነገር ቢኖር የምግብ ዘይት ነው፡፡ እንደሚታወቀው፣ አገሪቱ የራሷን የምግብ ዘይት በማምረት ለዜጎቿ ማቅረብ የምትችል ብተሆንም፣ የምግብ ዘይት ከውጭ እንደሚገባ ይታወቃል፡፡ ታዲያ እንዴት ነው በማለት ጥናቶችን ስከታተል፣ በቻይና ይህንን በተመለከት ያቀረቡትን የጥናት ውጤት አገኘሁ፡፡ ህም፣ ይህንስ ለወገን ማካፈል ጥሩ ነው አልኩ፡፡

ጥናቱ አላማ ያደረገው፣ በቻይና በሀገረ አቀፍ ደረጃ፣ የምግብ ዘይት አጠቃቀምና የስኳር በሽታ መከሰት ግንኙነት እንዳለው ለማየት ነበር፡፡ በሽታው የነሱም ችግር ነው ማለት ነው፡፡ እንደተለመደው በመረጃ የተደገፈ ጥናታዊ ግኝት ማቅረብ አስፈላጊ ነው፡፡

ባጠቃላይ 15 022 ዕደሜያቸው ከ20 አመት በላይ የሆኑ ዜጎች ከቻይና ኒውትሪሽን ሰርቬይ የተመለመሉ ሲሆን፣ እነዚህ ሰዎች በ1997፣ 2000፣ 2004፣ 2006 ወይም 2009 ተመልምለው እሰክ 2011 አ.ም ድረስ ክትትል ሲደረግ የቆዩ ናቸው፡፡ ሰዎች ወድ ክትትሉ ፕሮገራም ሲገቡ፣ የስኳር በሽታ እንደሌለባቸው አስመዝገበዋል፡፡

አነዚህ ሰዎች የሚጠቀሙት የምግብ ዘይት አይነቶች ማለትም ከጮማ የተሠራ ዘይት(lard oil)፣ የኦቾሎኒ ዘይት (Peanut oil)፣ ካኖላ፣ ሶይቢን፣ ሰሊጥ (sesame oil)፣ ከአትክልቶች ተጣርቶ የተሠራ ዘይት (refined blended plant oil) በየጊዜው ሪከርድ እንዲያዝ ተደርጎ፣ ሰዎች የሚጠቀሙት ወይም የሚመገቡት የዘይት አይነት አማካይ መጠን በስሌት እንዲታወቅ ተደረገ፡፡ የተለያዩ የስታቲሰቱክ መመርመሪያዎችን በመጠቀምና በማስላትም የስኳር በሽታ ቁጥር ሁለት መንስኤ ሰበብ ወይም ምክንያት ናቸው ወይም አይደሉም ለማለት አሁንም ሌላ ስሌት ተጠቀመው ውጤቱን አካፈሉን፡፡

አታካች የሆነውን ዝርዝር የስታቲሰቲክ ቁጥሩን ልለፈውና፣ የጥናቱን ማጠቃለያ ላጋራችሁ፡፡ በጥናቱ ወይም በክትትሉ ከነበሩ ሰዎች በ,ለ14 አመታት በተደረገው ክትትል 1014 ሰዎች የስኳር በሽታ ተከስቶባቸዋል፡፡

አጥኝዎቹ የሚሉት፣ ከጮማ የተሠራ ዘይት፣ የቦሎቄ ዘይት፣ ከአትክልቶች የተሠራ የተጣራ ዘይት መጠቀም ለስኳር በሽታ ቁጥር ሁለት መከሰት ከፍተኛ ምክንያት ናቸው፡፡ በአንፃሩ ሌሎቹን የዘይት አይነቶች የሶይቢን፣ የሰሊጥ፣ ካኖላ ዘይት ከስኳር በሽታ መከሰት ጋር ግንኙነት የላቸውም ይላሉ፡፡ የምግብ ዘይት መጠቀምን ቀንሱ የሚለው ምክር የመጣው፣ ዘይት የሚመገቡ ሰዎችን ጭራሽ ዘይት ከማይጠቀሙ ሰዎች ጋር በማወዳደር ያገኙትን ውጤት በመገንዘብ ነው፡፡ ዘይት የማይጠቀሙ ሰዎች እንዴት ነው፡፡ እንደዚሀ ከሆነ ዘይት ተወደደ ሲባል፣ የራሱ ጉዳይ ያስብል ይሆን?

ጥናቱ ለቻይኖችና ምክሩም ለቻይኖቹ ቢሆንም፣ ማካፈሉ ይበጃል፡፡ ባጠቃላይ የምግብ ዘይት አጠቃቀማቸውን እንዲቀንሱ ነው የሚመክሩት፡፡

 ከዚህ ቀደም ፍሩክቶስ የሚባል የስኳር አይነት ከስኳር በሽታ ጋር ግንኙነት እንዳለው በጎሽ ድረ ገፅ አስፍረያለሁ፡፡

ለማንኛውም የምተጠቀሙትን የምግብ ዘይት አይነት ማስተዋልም ጥሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምግብ ዘይት ከውጭ ማስገባቷ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ መንግሥት አስቦ ፖሊሲ እሰከሚቀይር መጠበቅም ተገቢ አይደለም፡፡ እንዳውም ህብረተሰቡ በረጋ መንገድ ጥያቄና ጫና በመፍጠር ፖሊሲ ማስቀየር ይኖበታል፡፡ ሀገር በቀል የሆኑ ዘይቶች ጤናማ እንደሆኑ ነው የሚገመተው፡፡

የስኳር በሽታ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ በከፈተኛ ቁጥር እየጨመረ 425 ሚሊዮን ሰዎች በሸታው ያለባቸው ሲሆን፣ ሌሎች 352 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ አደጋ ላይ ናቸው፡፡ ሌሎች ጥናቶችም የሚጠቁመት የአመጋገብና የአኗኗር ለውጥ ነው፡፡ የምዕራባውያን አመጋገብ መጠቀምና እንቅስቃሴ አለማዘውትር ችግር አለው፡፡

እንቅስቃሴ ውስጥ በእግር ረዘም ያለ መንገድ መሄድ ጠቀሚታም አለው፡፡ አግረኝነቱ ጥቅም አለው ማለት ነው፡፡ ለጤና ሲባል ቅርብ ቦታዎችና በአግር ማስነካቱ ገንዘብም ያድናል፡፡ ለማንኛውም፣ የስኳር በሽታ ሊከሰትብዎ የሚስችሉ ሰሌለት መሥሪያ ዘዴዎች በድረ ገፅ ቢኖሩም፣ በማን መመዘኛ ማን ይለካል የሚለውን ጥያቄ ማስተዋልም ተገቢ ነው፡፡ እንደምዕራባውያኑ የሚኖሩ ከሆነ፣ ሌላ ነገር ነው፡፡

መልካም ንባብ፡፡


ዋቢ

Zhuang et al, Cooking oil consumption and type 2 diabetes 1805

​የአዋቂ ስኳር በሽታ (Diabets Type 2) ላለባቸው ሰዎች ቡና እና አረንጓዴ ሻይ መጠጣት ዕድሜ ይጨምራል ወይ?
11/01/2020
 
ስለ ሁለቱ መጠጦች የተጠናውን ጥናት ውጤት ከማካፈሌ በፊት፣ ስኳር በሽታ ሲባል የትኛውን ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለብኝ፡፡ የስኳር በሽታ ብዙ አይነቶች ቢኖሩትም፣ በዋናነት የሚታወቁት ግን፣ በአሁኑ ጊዜ አይነት አንድና ሁለት የሚባሉት በእንግሊዝኛ (Tyep 1 and Tyep 2 Diabetes Mellitus) ተብለው የሚጠሩት ናቸው፡፡ በዚህ ርዕስ የምንጠቅሰው፣ ሁለተኛውን አይነት፣ ማለትም በአማርኛ የአዋቂዎች ብለን የምንጠራውን ነው፡፡ ለምን? ይኼኛው የሚከሰተው በልጅነት ሳይሆን በአዋቂ የዕድሜ ዘመን ውስጥ ባሉ ሰዎች ነው፡፡

ወደ ርዕሱ ስንመለስ፣ የምግብና የመጠጥ አይነቶችን በተመለከተ፣ በብዛት፣ ሰውነት ላይ ጉዳት የሚያመጡት ይታወቃሉ፡፡ ለሰውነት ጠቃሚ ናቸው የሚባሉም፣ በግምት ጓደኛና ጎረቤት ከሚያወሩት ውጭ በጥናት ብዙም አይወጡም፡፡ አሁን ግን ብቅ ብቅ አያሉ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ተጠንተው፣ ከበሬታ ባላቸው የሳይንስ መፅሔቶች ታትመው ለህዝብ ከሚቀርቡት መሀል፣ አንዱ የቡና ታሪክ ነው፡፡ ይህም ቡና መጠጣት በጉበት ላይ የሚያስከትለው ጤናማ ለውጥ ተደጋግሞ ሰለቀረበ፣ አሁን በመርህ ደረጃ፣ በጉበት ውስጥ ትርፍ ጮማ (Fatty Liver Disease) ላለባቸው ሰዎች በቀን አስከ ሶስት ኩባያ ቡና እንዲጠጡ በሀኪም ደረጃ ይመከራል፡፡ እኔም፣ ከሥራዎቼ አንዱ ሰለሆነ ይህንን ነገር በስፋት ለበሽተኞች ለመምከር እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ የመከርኩበትም ጊዜ አለ፡፡

ወደ ዋናው ርዕስ ስንመለስ፡ ቡና መጠጣትና ከሱም ጋር አብሮ አረንጓዴ ሻይ መጠጣት፣ የአዋቂ ስኳር በሽታ ላለባቸው ሰዎች ላይ ዕድሜ ይጨምራል ሲሉ፣ ከጃፓን በኩል ተመራማሪዎች ያቀረቡት ጥናት BMJ Open Diabetic Res Care በተባለ መፅሔት የወጣውን ነው የማቀርብላችሁ፡፡ ይህ መፅሄት፣ ከበሬታ ያለው ብቻ ሳይሆን፣ ከአሜሪካው የዳያቤትስ አሶሴሽን (ADA American Diabetes Association)ጋር በመተባበር ሰለሚሰራ፣ በዚህ መድረክ ታትሞ የወጣ የምርምር ጥናት በደንብ ታይቶ ተመክሮበት ነው እንዲታተም የሚደረገው በሚል ለአንባብያን እያቀረብኩ ነው፡፡ ሰለዚህ እንዲህ አይነት ነገር ለህዝብ ሲቀርብ፣ መታተሙ ሳይሆን እነማን ናቸው ጥናቱን ከፍተኛ ግምት ሠጥተው፣ በትክክለኛው መንገድ መጠናቱን አይተው የተቀበሉት የሚለውን መመልከት ከዛም እንደ መረጃ አድርጎ መቀበል ወሳኝ ነው፡፡ በድረ ገፅ የተቀመጠውን ሁሉ፣ ማንበብ ባይጎዳም ለመቀበል ግን አስቸጋሪ ነው፡፡

አጥኝዎቹ ያደረጉት የአዋቂ ስኳር በሽታ ያለባቸውን የ4923 ሰዎች መረጃ ነው የመረመሩት፡፡ ከነዚህ መሀል 2790 ወንዶች ነበሩ፡፡ አማካይ ዕድሜ 66 አመት ነበር፡፡ የክትትል ጊዜ በአማካይ 5.3 አመት ሲሆን፣ በዚህ አመታት ባሉ ጊዜ ውስጥ እነዚህ ሰዎች ቡናና አረንጓዴ ሻይ እንዴት እየጠጡ እንደነበር መረጃ ይሰበሰብ ነበር፡፡ ይህም ሰዎች ራሳቸው ሰለ ቡናና አረንጓዴ ሻይ አጠጣጣቸው መልስ የሚሠጡበት መጠይቅን በመሰብሰብ ነበር፡፡ ጥናቱ እየተካሄድ በጥናቱ ከታከተቱት መሀል 309 ሰዎች ሞተዋል፡፡

በጥናቱ ውጤት አድርገው ተመራማሪዎቹ ያቀረቡት፣ ቡና መጠጣት፣ ሻይ መጠጣት ወይም ሁለቱንም አንድ ላይ መጠጣት በአጠቃላይ ከሌሎች ጋር ሲወዳደር በማንኛውም ምክንያት የሚከሰተውን የሞት መጠን ከመቀነስ ጋር የተያያዘ ነው የሚል ነገር ነው፡፡ እዚህ ላይ ስታቲሰቲክስ በአሃዝ ሲገለፅ ትንሽ ግር የሚል ሁኔታ ቢፈጥርም፣ ድምዳሜው ተቀባይነት ያገኘው ደግሞ በስታቲስቲክስ ሰለተገለፀ ነው፡፡ እኔም እሱኑ ላቅርብላቸሁ፣ ወደፊት ግን መልመድ ይኖርብናል፡፡

በዚህ መሠረት

አርንጓዴ ሻይ የሚጠጡ ሰዎች ከማይጠጡት ጋር ሲወዳደር፣ አነሰ ቢባል በቀን እንድ ኩባያ የሚጠጡት ሰዎች ባጠቀቃይ የመሞት ሁኔታ አደጋው በአሃዝ (Hazard Ratio) 0.85 ነው፡፡ በቀን ሁለት ወይም ሶስት ኩባያ ሻይ ለሚጠጡ ሰዎች ደግሞ አደጋው ወደ 0.73 ይወርዳል፡፡ በቀን አራት ኩባያ ለሚጠጡ ሰዎች ደግሞ አደጋው ወደ 0.6 ይወርዳል ይላሉ፡፡ የኋለኛውን ግን ማሰብ ይከብዳል፡፡ በቀን አራት ጊዜ? ለማንኛውም ጃፓኖች ናቸውና አይገርምም፡፡ ባህልም ሳይሆን ይቀራል?

ወደ ቡናው ስንሄድ ደግሞ፣ በቀን ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ኩባያ ቡና የሚጠጡ ሰዎች ከማይጠጡት ጋር ሲወዳደር፣ የሞት አደጋው ወደ 0.59 (HR = 0.59, 95% CI, 042-0.82) ይወርዳል፡፡ ህም፡፡

አሁን የቀረው፣ ሁለቱንም የሚጠጡ ሰዎች ምን ተጠቀሙ የሚለው ነው፡፡ እንደ ጥናቱ ውጤት ከሆነ፣ ሁለቱንም እንጠጣለን ብለው መጠይቁን ለሞሉ ሰዎች ጭራሽ ቡናም ሆነ ሻይ ከማይጠጡ ሰዎች ጋር ሲነፃፀር ትልቁ ጠቀሚታ የታየው ሁለቱንም እንጠጣለን ብለው ለሞሉ ሰዎች ነው፡፡ በአሃዝ ሲገለፅ፣ በቀን ከሁለት አስከ ሶስት ኩባያ ሻይና በተጨማሪም ሁለት ኩባያ ቡና ለሚጠጡ ሰዎች የሞት አደጋው በግማሽ ቀንሷል፡፡ Hazard Ratio 0.49 (HR = 0.49, 95% CI, 024-0.99)፡፡ በሌላ በኩል፣ አራት ኩባያ ሻይና አንድ ኩባያ ቡና የሚጠጡ ሰዎች፣ በቀን ማለት ነው፣ Hazard Ratio የሚባለው ነገር (HR = 0.37 95% CI, 018-077) ወረደ ይላሉ፡፡

ለመሆኑ Hazard Ratio ማለት ምንድን ነው? አብሮት የሚገለፅ CI (Confidence Interval) የሚባል ነገር አለ፡፡ Hazard Ratio የበለጠ ተቀባይነት እንዲኖረው Confidence Interval የሚባለው ነገር በ95% ይገለፃል፣ ማለትም የታየው ለውጥ በተሰጠው ገደብ ውስጥ ለመሆኑ 95% ርግጠኛ ነው ለማለት ነው፡፡  በተለይ ግን በ Confidence Interval መሀከል ያለው የገደብ ስፋት ጠበብ ሲል Hazard Ratio ገላጭነቱ በጣም ያነጣጠረ ይሆናል ማለት ነው፡፡ Hazard Ratio የሚገልፀው፣ መድሀኒት ሆነ፣ በዚህ ጥናት እንደተጠቀሰው መጠጥ ወይም ምግብ ወይም ሌላ ነገር የወሰዱ ሰዎች ካልወሰዱ ሰዎች ጋር ሲወዳደር፣ የተጠቀሱትን ነገሮች በማድረጋቸው ያገኙት ጠቀሚታ ወይም ጉዳት መጠን በአሃዝ በስታቲስቲክ መግለጫ ነው፡፡ በዚህ ጥናት እንደታያው፣ ሻይ፣ ቡና ወይም ሻይና ቡና እንድ ላይ የሚጠጡት ሰዎች፣ ከማይጠጡት ጋር ሲወዳደር በተለያዩ ምክንያቶች የመሞት አጋጣሚው በሚጠጡት ሰዎች ላይ ቀንሶ መገኘቱ፣ የተገኘው የሞት አደጋ መጠን ደግሞ በምን ያህል እንደሆነ ነው የሚያሳየን፡፡ ለምሳሌ Hazard Ratio 0.5 ነው ቢባል፣ ቡናና ሻይ ጠጭዎች የሞት አደጋ ከማይጠጡት ጋር ሲወዳደር በግማሽ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ ይበቃል ሰታቲሰቲክ፡፡ የመፅሔቱ ሰዎች አይተው የተቀበሉትም ነገር ስለሆነ፣ በሳይንሳዊ መንገድ የተሰላም ሰለሆነ እኛን ከድካም ያድነናል ማለት ነው፡፡

እንግዲህ ከላይ እንደታየው፣ ጠቀሜታው ግልፅ ነው ቢባልም፡፡ ይህ ጥናት Observational Study ከሚባሉት ውሥጥ ሰለሆነ ስንቀበለው በጥንቃቄ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ፡፡ ጥቅም ታይቷልና ስኳር ያላበችሁ በሙሉ ጠጡ ከማለታችን በፊት፣ ቡናና ሻይ መጠጣት ችግር የሚያመጣበት ሁኔታ መኖሩንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የልብ ህመምና የደም ግፊት ባለባቸው ሰዎች ላይ ቡና መጠጣት ግፊቱንም ሰለሚጨምር አደጋ አለው፡፡ ሌላው፣ እንደ ቀላል እየታየ ነገር ግን ብዙ ችግር የሚያስከትለው ዕንቅልፍ ማነስ ወይም ማጣት ነው፡፡ ቡናና ሻይ ሲያዘወትሩ በዚያ በኩል የሚመጣውን አደጋ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ቡናና ሻይ ጠጡ የሚል ምክር ሲሰነዘር ደግሞ፣ ስኳር የሌለበት መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ አለዚያማ ትርፍም የለውም፡፡

ይህ እንግዲህ ሳይንሳዊ ውጤት ነው፡፡ ወደፊትም ለማጋራት ዝግጁ ነኝ፡፡ በነገራችን ላይ የAmerican Diabetes Association የጠቀስኩት ለዚህ ጥናት ውጤት ክብደት ወይም ተቀባይነት ከፍ እንዲል የዚህ ድርጅት የመፅሔቱ ተባባሪ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በአሜሪካ ስለ ስኳር በሽታ ህክምና ሆነ ምክር መመሪያዎችን የሚያወጣው ይህ ድርጅት በመሆኑ ነው፡፡ እኔ ካላመንኩበት ለናንተም አላቀርብ፣ ተገቢም አይደለም፡፡


Mereja: Komorita Y, Iwase M, Fujii H, et al. Additive effects of green tea and coffee on all-cause mortality in patients with type 2 diabetes mellitus: the Fukuoka Diabetes Registry. BMJ Open Diab Res Care 2020;8:e001252. doi:10.1136/ bmjdrc-2020-001252 

ፍሩክቶስ ኢንሱሊን የተባለ ሆርሞን ስራውን በደንብ እንዳያከናውን ምክንያት የሚሆነው የስኳር አይነት ነው፡፡ ኢንሱሊን በደንብ አለመስራት መቻል ደግሞ ከስኳር በሽታ መከሰት ጋራ የተያያዘ ነው፡፡

በአንስሳትም ሆነ በሰዎች ላይ በተፈጥሮ በሚገኘው ስታርች ከተባለ የስኳር አይነት ምትክ  ግሉኮስና ፍሩክቶስ በተባሉ የስኳር አይነተቶች መተካት የሚከተሉት ችግሮችን እንደሚያስከትል ነው፡፡

  1. ከሚገባው መጠን በላይ በፆም ጊዜ ኢንሱሊን የተባለው ሆርሞን ከፍ ብሎ መገኝት

  2. ሰውነት ለኢንሱሊን መሰጠት የሚገባውን የምላሽ ችሎታ መቀነስ

  3. በደም ውስጥ ከመጠን በላይ የስኳር መጠን መታየት ይህም በባዶ ሆድ ምርመራ ላይ ነው፡፡

  4. ለሰዎች የስኳር መጠን በሚሰጣቸው ጊዜ ጤናማ ያልሆነ የግሎኮስና የኢንሱሊን መጠን ከፍ ብሎ መገኘት

  5. ኢንሱሊን ስረውን ለመስራተ በሰውነት ሴሎች ውስጥ ዘልቆ ለመግባት የሚያስችለውንችሎታ መቀነስ


ሰዎች በተፈጥሮ የሚገኙ ምግቦችን በሚመገቡ ጊዜ በውስጣቸው መጠነኛ ፍሩክቶስ ቢኖርም ለለምሳሌ እንደየበሰሉ ፍራፍሬዎችነ በመመገብ ከጊዜ ብዛት ሰውነት የተላመደው በመሆኑ ችግር የማያሰከትል ሲሆን ፍሩክቶስ ከመጠን በላይ በመገኝባቸው በፋብሪካ የሚመረቱ ምግብና መጠጦችን በሚወስዱበት ጊዜ  ግን በተፈጥሮ የመላመድ ሁኔታው በመዛባት ችግር እንደሚያስከትል ነው፡፡ ይህም ማለት ሰውነተ ከለመደው በላይ ከፍተኛ የስኳር መጠን መጋለጡ ነው፡፡

በሰሜን አሜሪካ በግምት 75% የሚሆኑ ሁሉም የምግብና የመጠጠች አይነቶች ተጨማሪ ስኳር እንደሚደረግባቸው ነው፡፡

በ2010 ኢንሰቲቲዪት ኦፍ ሜዲሲን የተባለው ድርጅት ባወጣው የአመጋገብ መመሪያ በምግብና በመጠጥ ላይ የሚደረቡ ስኳሮችን ከሚገባው መጠን በላይ መጠቀም ሁለተኛውን አይነት የስኳር በሽታ እንደሚያስከትሉ ያሰረዳል፡፡

ለሰውነት ተገቢ የሆነው የስኳር መጠን ጠቅላላ ከሚወሰደው ካሎሪ 5 አስከ 10% በታች በመውሰድ ስኳር ከሚያሰከትለው መዘዝ መከላከል ይቻላል፡፡

የምንመገበውን የፍሩክቶስ መጠን በመቀነስ  ሰውነታችንን ከስኳር በሽታ እና ከሚያሰከትለው አሰከፊ ጉዳትና በልብና በደም ዝውውር ችግር ምክንያት ያለ ጊዜ ህይወት ማለፍን መከላከል ይቻላል፡፡

እንግዲህ ዋናው ምክር በፋብሪካ የሚመረቱ ምግብና መጠጦችን በመቀነስ በተፈጥሮ የሚያድጉ አትክልትና ፍራፍሪዎችን በመመገብ ለስኳር መንስኤ ሰበቡን ማስወገድ ይቻላል፡፡ ማሰተዋል የሚገባን ነገር ቢኖር በነዚህ የፋብሪካ ውጤት በሆኑ ምግብና መጠጦች ላይ የስኳር መጠናቸው ቢገለፅም ምን ያህሉ ፍሩክቶስ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ የፍሩክቶስ መጠን እንዲገልፁ የሚያሰገድድ ህግ የለም፡፡ ወደ ሰባት የሚሆኑ የአመጋግብ መመሪያዎች በተፈጥሮ የሚገኙ ምግቦችን መመገብ አንጂ ስኳር የተጨመረባቸውን የፋብሪካ ምርቶች እንዳይመገቡ ይመክራሉ፡፡

መረጃዎች አንደሚዘግቡት የዳያቤትስ ወይም የስኳር በሽታ እንደወረርሽኝ መከሰት ለአመታት እየጨመረ የመጣው የአሜሪካኖች ከመጠን በላይ ስኳርን ከመመገብ ጋራ የተያያዘ ነው፡፡ በወገኖቻችንም ላይ ስኳር በሽታ ቁጥር ከፍ እያለ መታየቱ ግልፅ ነው፡፡  በማጠቃለልም ለሰውነታችን በተፈጥሮ ከምንመገበው ምግብ ላይ ተጨማሪ ስኳር አያስፈልገውም፡፡  በተለይም ፍሩክቶስ ያለባቸው ምግቦች፡፡ ምናልባትም ስኳር ባልተጨመረበት ምግብ ያደጉ ሰዎች በዚህ በተለያየ መልኩ ስኳር የተጨመረባቸውን ምግብና መጠጦችን መጠቀም ሰውነት ያልመደውና የማያውቀውነ ነገር ማጋለጥ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተራው የስኳር በሽታ መዘዝ መሆኑ ነው፡፡  ወደ ሁዋላ ወደ ተፍጥሮ ምግቦች መመለሱ ይበጃል፡፡