​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

እህል አጥቂውን ያጠቃል

ስለ ቅድመ ስኳር ወይም (Prediabetes ) ስለሚባል ክስተት ከዚህ በፊት በጎሽ ድረ ገፅ ፅሁፍ አስቀምጠን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በቅርብ ጊዜ በእንግሊዝ አገር የህክምና መፅሄት የቀረበን የጥናት ውጤት ለማከፈል እንወዳለን፡፡ ከዚህ ቀደም በቀረበ ፅሁፍ የስኳር ኢንዱሰትሪ ረቀቅ ባለ መንገድ ነብሳቸውን ከሸጡ ሳይንቲሰቶች ጋር በመሆን ለልብ ህመምና ሌሎች ችግሮች ተጠያቂ ምግብ ጮማ ነው በማለት ለአመታት በየመጠጡና በየምግቡ በፋብሪካ የተመረተ ስኳር በመጨመር ሲሽጡ መክረማቸው ግልፅ ነው፡፡ እንደ ትምባሆ ሁሉ ይህ በፋብሪካ የሚመረት ከመጠን በላይ የሆነ ስኳር ለስኳር በሽታ መንስኤ መሆኑን በድረ ገፃችን አስፍረናል፡፡ ሰሞኑን በቴሌቢዢን ከትልልቆቹ ለስላሳ መጠጥ አምራቾች የአንዱ ሥራ አስኪያጅ ያለ ሀፍረት እንዲህ ሲሉ ታይተዋል፡፡ ወደፊት የምናመርታቸው መጠጦቻችን የስኳር መጠናቸውን ቀንሰን አነስ ያለ መጠን ያለቸው እንዲሆኑ እየተዘጋጀን ነው በማለት አንድ ጥሩ ወሬ እየነገሩን ነው፡፡ ልብ ብሎ ላዳመጠና ለተመለከተ ሰው፤ ማክዳኖልድ ፍሩክቶስ የተባለው የስኳር አይነት በብዛት ያለባቸውን የምግብ አይነቶች ከሽያጭ መደርደሪያ እንደሚያወርዱ አስታውቀዋል፡፡ እንግዲህ የለስላሳ መጠጥ ሥራ አስኪያጇም የስኳር መጠን እንቀንሳለን ሲሉ፤ ፊት ለፊት ባያምኑም ስኳር ጉዳት እንደሚያሰከትል ያውቃሉ፡፡

ለማንኛውም በአማርኛ አባባል፡ ሶዳ የሚባል ቅጠል በደጃፊ አይበቀል ማለት ጥሩ ሳይሆን አይቀርም

ወደ ጥናቱ ልመልሳችሁና፡፡ የስኳር በሽታ ከመከሰቱ በፊት ቅድመ ስኳር የሚባለ ሁኔታ አለ፡፡ ሰዎች ካልተጠነቀቁና አስፈላጊውን ርምጃ ካልወሰዱ የስኳር በሽታ በገሀድ መከሰቱ አይቀርም፡፡ ከበሽተኞቻችን ጋር ስንወያይ፣ ጥያቄው ምን አይነት ምግብ ቢሆን ይሻላል ነው፡፡ ሀኪሞችም ብንሆን ስንቱን ምግብ ከልክለን እንችላለን? ይህ ጥናት ታትሞ ሲወጣ በጥሩ መንፈስ ነው የተቀበልነው፡፡

ባጠቃላይ ከፍተኛ የፕሮቲን መጠንና መጠነኛ የሆነ የካርቦሀይድሬት ምግብ የቅድመ ስኳር ሁኔታን ያሻሻለ መሆኑን ጥናቱ ይዘግባል፡፡

ይህ ጉዳይ ለምን አሳሳቢ እንደሆነ ለመረዳት በአሜሪካ ብቻ ወደ 86 ሚሊዮን የሚሆነ ሰዎች ቅድመ ስኳር ሁኔታ አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን አሳሳቢ በሆነ ደረጃ የስኳር በሽታ ሲከሰት ነው የሚታየው፡፡

ጥናቱ መጠነኛ ቁጠር ያለቸው ሰዎች የተሳተፉበት ቢሆንም ውጤቱ በጣም ገላጭ ነው፡፡ የተደረገው ነገር 24 አዋቂዎችን ከሁለት ወገን በመክፈል፤ አንዱ ወገን ከፍተኛ ፕሮቲን መጠን ያለበት (30 ፐረሰንት ፕሮቲን፣ 30 ፐርሰንት ጮማ ፣ 40 ፐርሰንት ካርቦሀይድሬት) ሌላው ወገን ደግሞ ከፍተኛ ካሎሬ ያለበት (15 ፐርሰንት ፐሮቲን፣ 30 ፐርሰንት ጮማ፣ 55 ፐርስንት ካርቦሀይድሬት) የተዘጋጁ ምግቦችን ለስድስት ወራት መመገብ ተጀመር፡፡ ጥናቱ ከመጀመሩ በፊትና ከስድስት ወር በኋላ የደም ምርመራዎች ተደረጉ፡፡

ቅድመ ስኳር የመሻል ወይም መሻር ምልክት የተባሉት ፤ ምግብ ሳይበሉ (ሰምንት ሰአት ፆም) በሚደረግ ደም ምርምራ የስኳር መጠን ከ100 mg/dl በታች መሆንና፤ ግሉኮስ ጠጥተው ከሁለት ሰአት በኋላ በሚደረግ ምርመራ መጠኑ ከ140 mg/dl በታች ሲሆን ነው፡፡

የጥናቱ ውጤት ያሳየው፡ ከፍተኛ ፕሮቲን ያለው ምግብ የተመገቡ ሰዎች በአስራሁለቱም ሙሉ በሙሉ የቅድመ ስኳር ሁኔታ መሻር ታይቷል፡፡ በቀሪዎቹ አስራ ሁለት ሰዎች ውስጥ አራቱ ብቻ ላይ ነው ይህ የመሻሻል ሁኔታ የታየው፡፡ በስታቲክሳዊ ስሌት ይህ ውጤት መሠረት ያለው ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ሄሞግሎቢን A1c(HbA1c) በሚባል ምርመራ ከፍተኛ ፕሮቲን የተመገቡ ሰዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ መጠኑ ዝቅ ሲል ተከስቷል፡፡ ይህ ምርመራ በደም ውስጥ የስኳር መጠን ለዘጠና ቀናት እንዴት አንደነበር የሚገልፅ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ ፕሮቲን የተመገቡ ሰዎች ኢንሱሊን የተባለው ሆርሞን በደንብ መስራት የሚችልበት ሁኔታ ተሻሽሎ የታየ ሲሆን፤ ለልብ ህመም አደጋ የሚያገልጡ ሁኔታዎች መሻሻልን ጨምሮ የኮለስትሮልና ሌላ የጮማ መጠን መቀነስና፤ ለልብ ህምም የሚዳርጉ በሰውነት የሚፈጠሩ አስጊ ኬሚካሎች መቀነስ ከፍተኛ ካሎሪ ከተመገቡት ሰዎች በላይ በተሻለ ሁኔታ ታይቷል፡፡

መርጠን ካልተመገብን እህል አጥቂውን ያጠቃል ወደሚለው አባባል መመለሳችን ነው፡፡ ሰለዚህ ኩኪዎች፣ ለስላሳ መጠጦች፤ ከፋብሪካ የሚመጡ ጭማቂዎችን ደህና ሰንብቱ ብሎ ወደ ፍራፍሬና አታክልት፣ ሥጋ፣ አሳ የመሳሰሉትን መመገብ ጥሩ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ዳቦ ከካርቦሀይድሬት ወገን ነው የሚመደበው፡፡ በየቀኑ የምንወስደውን የስኳር መጠን መቀነስ አስፈላጊ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አልኮሆል ማለት የመጨረሻ ውጤቱ ስኳር ነው፡፡ ስለዚህ ስሌቱ ውስጥ ማሰገባት ተገቢ ነው፡፡ ስኳር ተወደደ ማት ጥሩ ወሬ ነው፡፡ ቢቀርስ፡፡ 



በደም የስኳር መጠን

 ደረጃ (ትርጉም)          

 Hgb A1c (percent) 

Fasting blood glucose (mg/dl) 

Oral glucose tolerance test (mg/dl)  

ጤናማ


Below 5.7



99 or below


139 or below  

ቅድመ ሰኳር በሽታ


5.7 to 6.4   100 - 125140 - 199
 የስኳር በሽታ
6.5 or           above           126 or above

200 or above


Adapted from American Diabetes Association


የደም ምርመራ ሲያደርጉ
የስኳር መጠን ቁጥር ጤናማው ምን ያህል ነው?


Pre diabetes ቅድመ ስኳር በሽታ

ምልክት ሳይሠጡ ሳያስጠነቅቁ እያዋዙ ብቅ ከሚሉ በሸታዎች አንዱ የስኳር በሽታ ነው፡፡ በመረጃ በአሃዝ እንደሚታየው በዚህ በሽታ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሄዱ ግልፅ ነው፡፡ አደጉ በሚባሉ አገራት አዋቂ ከሆኑ በኋላ፣ የስኳር በሽታ የሚከሰትባቸው ሰዎች ባሕርይ ለየት ያለ ነው፡፡ ያም በተለይ በሰውነት ገዘፍ ያሉና፣ ሰውነታቸው ላይ ያልተስተካከለ ውፍረት የሚታይባቸው ሰዎች ላይ ነው፡፡ በአገር ቤት ግን የተለየ ነው፡፡ እኔም እንደ ሕክምና ባለሙያ በአእምሮዬ የሚመላለሰው ለምን ይሆን በአገር ቤት የስኳር በሽታ በብዛት የሚከሰተው፣ ከተከሰተም ደግሞ በሰውነት ገዘፍ ያላሉ ሰዎች ላይ ነውና ምክንያቱ ምን ይሆን የሚለው ጥያቄ ነው፡፡


ታዲያ ነገሩ እንዲህ ከሆን፣ የስኳር በሽታ ማን ላይ መከሰት እንደሚችል አስቀድሞ የሚጠቁም ምልክት ወይም ምርመራ ሰለሌለ፣ ሁሉም ሰው ሰለዚህ የስኳር በሽታ ግንዛቤ ማግኘትና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት በሚል ትምህርት በተከታታይ ለማቅረብ ፈለግሁ፡፡


እያንዳንዱ ሰው ማስተዋል የሚገባው ነገር፣ ዋናው የስኳር በሽታ ከመከሰቱ በፊት ቀደም ብሎ እንደ ማስጠንቀቂያ የሚታይ፣ ለዋናው የስኳር በሽታ ዋዜማ የሚመስል ቅድመ ስኳር የሚባል ሁኔታ መኖሩን ነው፡፡ በአንግሊዝኛው አጠራር Pre diabetes ይባላል፡፡


ሰለዚህ ሁኔታ አንዳንድ እንበል፤


ይህ ሁኔታ እንግዲህ፣ ምንም ምልክት ወይም ስሜት አይሰጥም፡፡ በደም ውስጥ የስኳር መጠን ሲለካ፣ መጠኑ ከፍ ያለ ሆኖ ግን የስኳር በሽታ የሚባል ደረጃ ሳይደርስ ሲቀር ነው፡፡ በቂ ክትትልና ጥንቃቄ ካልተደረገ፣ ይህ ሁኔታ በአስር አመታት ወይም ባነሰ ጊዜ ውስጥ ወደ ስኳር በሽታ ይሻገራል፡፡ ይህ ቅድመ ስኳር በሽታ በታየበት ጊዜ ምልከት ባይሰጥም፣ ክስኳር በሸታ ጋር ተያይዘው ብቅ የሚሉት የልብና የደም ሥር በሸታዎች አብረው በጊዜ እየጀመሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰለዚህ ማስጠንቀቂያነቱ ከስኳር በሽታ ያለፈ ሰለሆነ በቂ አትኩሮት ሊሠጠው ይገባል፡፡


ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ይህንን ጉዳይ ቀደም ብለው ከነቁበት፣ ጤንነትዎን በመንከባከብ፣ ዋናው የስኳር በሽታ እንዳይከሰት የማድረግ ዕድል አለዎት፡፡ ያም አንግዲህ፣ ጤናማ አመጋገብ፣ መደበኛ የሆነ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጤናማ የሰውነት ክብደት በመጠበቅ በደም የሰኳር መጠን ዝቅ እንዲል ማድረግ ይችላሉ፡፡
ቅድመ ስኳር ምንም ምልክት ላይኖረው ቢችልም፣ በቆዳ ላይ የሚታይ አንድ ምልክት ግን ከዚህ ሁኔታ ጋር ሊያያዝ ይችላል፣ በተጨማሪም ለስኳር በሽታ መከሰት ምልክት ይሆናል የሚባል ነው፡፡ በቆዳ ላይ ጠቆር በማለት በጉልበት፣ በክርን፣ በአንገት፣ በብብት፣ የእጅ ጣቶች ላይ የሚታይ ነገር ነው፡፡ ለማንኛውም ይህ ምልክት ኖረም አልኖረም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ቅድመ ሰኳር ሁኔታው ደግሞ ወደ ስኳር በሽታ ከተሸጋገረ የሚታዩ ምልክቶችና ስሜቶች አሉ፡፡ እነሱም፣ የውሀ ጥም መጨመር፣ ቶሎ ቶሎ ሽንት መሽናት፣ ድካም ስሜት፣ አይን ብዥ ማለትን ያካትታሉ፡፡ ይህ አይነት ስሜት ጤናማ ስላልሆነ ወደ ሀኪም መሄድ የግድ ይሆናል፡፡


ለመሆኑ ለቅድመ ስኳር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች አሉ ወይ? እነዚህን ሀኔታዎች በጥሞና መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ቤተሰብ ወይም ጓደኛን መምከርም አስፈላጊ ነው፡፡

ሁኔታዎቹ፤

  • የሰውነት እንቅስቃሴ የማያዘወትሩ ከሆነ
  • የሰውነት ክብደት ከመጠን በላይ ካለፈ
  • ዕድሜ ከ45 አመት በላይ ከተሻገረ
  • በቤተሰብዎ ውስጥ ዋናው የስኳር በሽታ ያለበት ሰው ካለ
  • አፍሪካዊ ዝርያ ካለብዎት
  • በሴቶች በኩል፣ ከዚህ ቀደም ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የስኳር በሽታ ተከስቶ ከሆነ፣ የተወለደው ልጅ ከዘጠኝ ፓውንድ ወይም ከ4.1 ኪሎ ግራም በላይ ከሆነ
  • የደም ግፊት ካለብዎት
  • እንደገናም በሴቶች በኩል፣ polycystic ovary syndrome የሚባል ሁኔታ ካለባቸው፣ (ሁኔታው የወር አበባ መዛባት፣ በሰውነት ላይ ከሚገባው በላይና በሴቶች ላይ መብቀል የማይገባበት ቦታ ፀጉር ሲበቅል፣ ከመጠን በላይ ውፍረትን የሚያካትት ነው፡፡)
  • ኮለሰተሮል መጠን ደግሞ፣ ጤናማ (HDL) የሚባለው የኮለስትሮል መጠን ከፍ ማለት ሲገባው በማነስ ከ35 በታች ሲሆንና፣ ትራይግላይሰራይድ (Triglyceride) የሚባለው በደም የሚለካ የጮማ መጠን ከ 250 በላይ ሲሆን
  • እንቅልፍ ደግሞ ትንሽ ወይም ከመጠን በላይ ሲሆን፣ ማለትም፣ ከስድስት ሰአታት በታች የሆነ በቂ ዕንቅልፍ አለማግኘት፣ አለዚያም ከበቂ በላይ ወይም ከዘጠኝ ሰኣታት በላይ የሚተኙ ከሆነ

እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ካሉብዎት፣ ለቅድመ ስኳር አጋላጭ ሰለሆኑ፣ ወደ ሀኪምዎ ጎራ ብለው ምርምራ እንዲረግ መጠየቅ አለብዎት፡፡ በዚህ አጋጣሚ፣ ለዚሁ ሲሉ ወደ ሀኪም የሚሄዱ ከሆኑ፣ ለስምንት ሰአታት ሳይመገቡ በባዶ ሆድ መሄድ ምርምራው ባንድ ቀን እንዲጠናቀቅ ይረዳዎታል፡፡ ከመመላለስ አይሻልም ወይ?


ስለ ላቦራቶር ምርመራዎች፡


A1c Test (Hemoglobin A1c, Hgb A1c) ይህ የደም ምርመራ፣ የስኳር በሽታ ለማወቅና ለመከታተል፣ በተጨማሪም ቅድመ ስኳር ሁኔታ መኖሩን ለማወቅ የሚሠራ ነው፡፡ ከላይ ሠንጠረዡን ይመልከቱ፡፡ ብቻውን ወይም ከሌሎች ምርመራዎች ጋር አብሮ ይሠራል፡፡ ለዚህ ምርመራ ባዶ ሆድ መሆን አያስፈልግም፣ በማንኛውም ጊዜ መሠራት ይችላል፡፡ መጠኑ የሚጠቁመው፣ በቀይ የደም ሴሎች ውስጥ በሶሰት ወራት ውስጥ የነበረውን አማካኝ የስኳር መጠን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የስኳር በሽታው ላለባቸው ሰዎች፣ የስኳር መጠኑ በቁጥጥር ሥር እንደሆነ ለማሳየት ለክትትል ይታዘዛል፡፡


Fasting blood glucose (FBS) ይህ ደግሞ በባዶ ሆድ ማለትም ለስምንት ሰኣታት ምግብ ሳይበሉ የሚሠራ የደም ምርመራ ነው፡፡ በተለይም በጠዋት ከተሠራ ጥሩ መረጃ ይሠጣል፡፡


Oral glucose tolerance test (OGTT) ይህ ምርመራ ባሁኑ ጊዜ ለነብሰ ጡር ሴቶች የሚታዘዝ ነው፡፡ ምርመራው የደም ሲሆን፣ ስኳር በአፍ ከተወሰደ በኋላ ጊዜ እየጠበቁ ደም በመውሰድ የስኳር መጠኑን በመለካት የሚሠራ ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት የምርመራ አይነቶች ጠንከር ያለ መረጃ ወይም የተሻለ መረጃ ይሠጣል፡፡ ምርመራው ውስብስብ ያለ ነው፡፡ ሰዎች ባዶ ሆድ (ስምንት ሰአታት) ከሆኑ በኋላ፣ 75 ግራም ስኳር በውሃ ተበጥብጦ እንዲጠጡ ይደረግና፣ ከሁለት ሰአታት በኋላ በደም ምርመራ የስኳር መጠን ይለካል፡፡ ሰለአተረጓጎም ሠንጠረዡን ይመልከቱ፡፡