​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

አዲስ የኮቪድ መዘዝ፣
በኮቪድ መያዝ፣ ዕድሜያቸው ከ18 በታች የሆኑትን ለስኳር በሽታ ያጋልጣል


ያሁኑ ይባስ እንደሚባለው፣ በፍጥነቱ እሰካሁን ያልታየ መላው አለምን ያጥለቀለቀው ኦሜክሮን ለካበድ ህመምና ለሞት ቀደም ብለው ከታዩት ዝርያዎች ሻል ያለ ነው ቢባልም፣ በንፅፅር ነው እንጂ አሁን ቢሆን ሰዎች እየሞቱ፣ ሆስፒታል እየገቡ፣ የሆስፒታል አገልግሎት ከፍተኛ ጫና እየታየበትም ነው፡፡
አሁን በቅርቡ ለህትመት የበቃን ጥናት ላካፍላችሁ፡፡ ኮቪድና ልጆችን በተመለከት፣ ከዚሀ ቀደም እነሱ ብዙ አይያዙም የሚለውን አባባል አሜክሮን አክሽፎታል፡፡ ሕምም አይጠናባቸውም ይባላል፣ በርግጥ ያም ይታያል፡፡ ነገር ግን የሚያዙ ልጆች ቁጥራቸው በመብዛቱ ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ልጆችም ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡፡
በጣም አሳሳቢ ሆኖ የተገኘው ግን፣ ወጣቶቹ ወይም ልጆቹ በኮቪድ ተይዘው በቀላሉ ካፉት በኋላ እየተከሰተ ያለ ለዕድሜ ልክ የሚሆን ሌላ በሽታ እየታየባቸው መሆኑ ነው፡፡ ይህ በሽታ ደግሞ የስኳር በሽታ ነው፡፡
በጃንዋሪ 7፣ በአስቸኳይ ለህዝብ እንዲቀርብ የተደረገው Morbidity Mortality Weekly Report (MMWR) ዘገባ፣ እድሜያቸው ከ18 አመታት በታች የሆኑ ልጆች፣ ኮቪድ ከተያዙ ከ30 ቀን በኋላ፣ በኮቪድ ካልተያዙት ጋር ሲወዳደር፣ ተይዘው የነበሩት አዲስ የስኳር በሽታ እንደሚነሳባቸው ነው የሚገልጠው፡፡ ለምን እንዲህ ሆነ ብሎ መጠየቁ አይቀርም፡፡ በመላ ምት ደረጃ፣ ይህ ኮሮና የተባለ ቫይረስ መላው የሰውነት ክፍልን ሰለሚወር፣ በ
ደም ውስጥ ሰኳርን ለመቆጣጠር አሰፈላጊ ሆርሞን የሚያመነጨውን ፓንክሪያስ የተባለ የሰውነት ክፍል ሰለሚጎዳ ነው የሚል ነው፡፡
በኮቪድ ምክንያት በልጆች ላይ ዘግየት ብለው ከሚታዩ ሁለት በሽታዎች በተጨማሪ፣ ይህ የሰኳር በሽታ መከሰት ሶሰተኛ መሆኑ ነው፡፡ የስኳር በሽታ ሁለት አይነት አለው፣ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ይባላሉ፡፡ በልጆቹ ላይ የተከሰተው ቁጥር አንድ አይነቱ ነው፡፡ ይሀም በአዋቂዎች ላይ እንደሚከሰተው አይነት ሁለት እንደሚባለው በኪኒን ብቻ የሚቆጣጠሩት ሳይሆን፣ በመርፌ በኩል በሚሰጥ የኢንሱሊን መድሐኒት ነው ህክምናው የሚቀጥለው፡፡
ይህ እንደ አዲስ የሚከሰት ሲሆን፣ የስኳር በሽታ መሆኑ ሲታወቅ ልጆቹ የስኳር መጠናቸው ከልክ በላይ ሆኖ፣ ሰውነታቸው ከሚገባው በላይ አሲድ ጨምሮ ነው የሚገኙት፡፡ ይህ አሲድ ደረጃ መድረስ፣ የስኳር በሽታ የከፋ ደረጃ መድረስ ውጤት ነው፡፡
ይህ ጉዳይ ቀደም ብሎ በአውሮፓ፣ በልጆ ላይ እንደታየም ተዘግቧል፡፡ ጥናት የተደረገው ከማርች 1 2020 ጀምሮ እከሰ የካቲት 26 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን፡፡ ከ18 አመት በታች የሆኑ ልጆችን ከሁለት በመመደብ፣ በኮቪድ ያልተያዙና በኮቪድ ተይዘው ከነበሩ መሀከል አዲስ የስኳር በሽታ በየትኛው ወገን በብዛት ታየ ለሚል ጥያቄ መልስ ለመስጠት ከሰበሰቡት መረጃ ያገኙትን ውጤት ነው ያካፈሉት፡፡ መረጃዎች ከሁለት ቦታ የተሰበሰቡ ሲሆን፣ በጥናቱ ውጤት መሠረት፣ ካንደኛው መረጃ የታየው፣ አዲስ የስኳር በሽታ መከሰት በኮቪድ ተይዘው በነበሩ ወጣቶች ካልተያዙት ጋር ሲወዳደር በ166 ፐርሰንት በልጦ የታየ ሲሆን በሌላኛው መረጃ ደግሞ በ31 ፐርስነት በልጦ ታይቷል፡፡ የዚህ ጥናት ውጤት ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም በአዋቂዎች ላይ በኮቪድ ከተያዙ በኋላ በስኳር በሽታ የመያዝ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ ከተገለጠው መረጃ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አሁን በልጆቹ መከሰቱ ታወቀ እንጂ ባዋቂዎች በኩል፣ ከኮቪድ በኋላ ስኳር በሽታ ተከትሎ የመምጣጥ ሁኔታ ከፍ ያለ ነው፡፡
በኮቪድ ተይዘው በጠና ባይታመሙ፣ ሆስፒታል ባይገቡና ሕይወታቸው ባያልፍም፣ ለዕድሜ ልክ የሚሆን የስኳር በሽታ መከሰት፣ ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ የስኳር በሽታው የትኞቹ ልጆች ላይ ነው የሚከሰተው ለሚለው ጥያቂ፣ ከዚህ በፊት ቅደም ስኳር የሚባል ሁኔታ በነበራቸው ወጣቶች ላይ ከፍ ብሎ ቢታይም በሌሎች ላይ ሊከሰት እንደሚችል ይታወቃል፡፡
ይህ አደጋ፣ የሚያስረዳን ነገር ቢኖር በኮቪድ ላለመያዝ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ፣ የመከላከያ መንገዶችን ጨምሮ ክትባቱን በመውሰድ በቂ ጥንቃቄ እንዲደረግ ነው ምክሩ፡፡ ወላጆችም ልጆቻቸው ከኮቪድ በኋላ ለዚህ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ በመገንዘብ የመከላክል ተግባሩን ጠበቅ ማድረግና፣ ልጆቹን (ክትባት ባለበት አገር) የኮቪድ ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ እንግዲህ ኮቪድ ተራ ጉንፋን ወይም ኢንፍሉዌንዛ እንዳልሆነም መገንዘብ አለብን፡፡ የሚሻለው ነገር አለመያዙ ነው፡፡