ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ
Community health
education in Amharic
ሳይነከሱ በውሻዎ ወይም በድመትዎ አማካኝነት በሽታ መያዝ
ይህ፣ በነገራችን ላይ አዲስ ግኝት ነው፡፡ በጁን 24 በሳን ፍራንሲስኮ ከተማ በተካሄደ አመታዊ የማይክሮባዮሎጂስቶች ስብሰባ ላይ የቀረበ ባለሙያተኞችን ያስገረመ ነገር ነው፡፡ አሁን ግን ውሻ ያላቸው ሰዎች ሊያውቁት የሚገባ ነገር በመሆኑ ለጎሽ ድረ ገፅ አንባብያን ለማቅረብ ፈለግሁኝ፡፡ የውሻ በሽታ ሲባል ሬቢስ (Rabies) ለመጥቀስ አይደለም፡፡ ሌላ ከውሾች አፍ ውስጥ የሚገኝ ፓሰቼሮላ መልቶሲዳ (Pasteurella multocida) በሚባል ባክቴሪያ ስለሚመጣ በሽታ ነው፡፡ ይህ ባክቴሪያ ወደ ሰዎች ሰውነት ዘልቆ በሽታ የሚያስከትለው፣ ሰዎች በውሻ ወይም በድመት ሲነከሱ ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ፣ የተነከሱ ሰዎች ወደ ህክምና ሰለሚሄዱ ህክምናም ስለሚያኙ በበሽታው አይያዙም፡፡ ነገር ግን ወደ ህክምና ከሄዱ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡
አዲስ ግኝት የሆነው፣ ከተለመደው ከውሻ ንክሻ ውጭ ሰዎች በባክቴሪያው ተለክፈው መገኘታቸው ነው፡፡ እንደተመራማሪዎቹ ግኝት፣ አዲስ የመለከፊያ መንገድ ሆነው የተገኙት፤ ሰውነታቸው ላይ ቁስል ያላቸው ሰዎች በውሻ ምራቅ አማካኝነት ከዚያም በተጨማሪ (ማን ይህን እንደሚያደርግ ባይገባኝም) ከውሻ ጋር አብሮ መብላት ናቸው፡፡
ይህ ጥናት እንዲካሄድ ሰበብ የሆነው፣ በፔንስልቫኒያ፣ የሴንት ሉክ ሆስፒታል፣ የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ የሆኑ ሀኪም በአንድ በሽተኛቸው ላይ ባዩት ያልተለመደ ሁኔታ ነው፡፡ ሀኪሙ ዶ/ር Don Walter Kannangara ይባላሉ፡፡ በሽተኛቸው የስኳር በሽታ ያለበት ሲሆን፣ በከፍተኛ ትኩሳትና የብርድ ብርድ ስሜትና ማንቀጥቀጥ ጋር ሆስፒታል ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም ሰውነቱ ላይ ቁስል ሰለነበረበት፣ ቁስሉ ላይ በተደረገው ምርመራ ሌላ ባክቴሪያ ተገኝቶበት ሰለነበር፣ ያው አሁን የታመመበት ምክንያት በቁስሉ ላይ በተገኘው ባክቴሪያ ሊሆን ይችላል ተብሎ ነበር የተገመተው፡፡ ነገር ግን የበሽተኛው ደም ተወስዶ ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ፣ ደሙ ላይ በካልቸር blood cultures ፣ ፓሰቼሮላ መልቶሲዳ የተባለው ባክቴሪያ ይገኛል፡፡ ህም፣ ሰውየው በውሻ ተነክሶ አያውቅም፡፡ ነገር ግን፣ ራሱ በሽተኛው እንደገለፀው፣ ሲያስታውስ፣ የአግሩ አውራ ጣት ላይ ትንሽ ቁስል ነበረውና ያችን ቁስል ውሻው እንደላሰለት ይናገራል፡፡ በተከሉት ወራት፣ ሀኪሙ ሁለት ተመሳሳይ ሁኔታዎች ማለትም ሳይነከሱ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ያገኛሉ፡፡ ከንክሻ ውጭ በሌላ መንገድ በፓሰቼሮላ መልቶሲዳ የተለከፉ ሰዎች ለህይወት አስጊ የሚደርስ ህመም ላይ እንደሚውድቁ ይታወቃል፡፡ በዚህ ጊዜ ሀኪሙ የሚመለከታቸውን ሀላፊዎች ካስፈቀዱ በኋላ፣ ጥናት ይጀምራሉ፡፡
በጥናታቸው መሠረት፣ ባለፊት 30 ወራቶች፣ የህሙማን ፋይሎች ሲያገላብጡ፣ 79 ሰወች በባክቴሪያው ተለክፈው ህክምና የተደረገላቸው መሆኑን ያገኛሉ፡፡ እነዚህ 79 ሰዎች በደማቸው ውስጥ ፓሰቼሮላ መልቶሲዳ የተገኘባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በጥናቱ መሠረት፣ ከ79 መሀል አብዛኞቹ በዕድሜ የገፉ ማለትም 63.1 ፐርሰንቱ ከ50 እስከ 80 አመት የሆነቸው ሲሆኑ፤ መተላለፊያ መንገዱ ሲታይ፣
ከ79 መሀል አርባ አምስቱ በንክሻ አማካኝነት ማለትም 29 በድመት ንክሻ፣ 16 ደግሞ በውሻ ንክሻ አማካኝነት ነው፡፡ የቀሩት 34 ግን በንክሻ አማካኝነት አልነበረም፡፡ ይህ ነው እንግዲህ እንዴት ሆኖ የሚለውን ጥያቄ ያስነሳው፡፡ ከነዚህ መሀል በዝርዝር ሲታይ መተላለፊያ መንገዱ የሚከተለው ሆኖ ነው የተገኘው፤
እንግዲህ በንክሻ አማካኝነት ሳይሆን በሌላ መልክ በባክቴሪያው የተለከፉ ሰዎች ለህይወት አስጊ ደረጃ የሚደርስ ህመም ስለሚይዛቸው፣ ውሻና ድመት ያላቸው ሰዎች ሊያደርጉት ወይም ሊከተሉት የሚገባው ምክር፣ ሰዎች ሰውነታቸው ላይ ቁስል ካላቸው፣ ቁስላቸው በደንብ መሸፈን እንዳለባቸው ነው፡፡ እንዳየነው፣ ከውሻ ለሀጭ፣ ከድመት ፀጉርና አይነምድር ጋር ንክኪ እንዳይኖር ነው፡፡ የሰውነት የመከላከያ አቅም የከሰመባቸው ሰዎች፣ ኤይድስን ጨምሮ በጭራሽ ከድመትና ውሻ ጋር እንዳይገናኙ የሚል የሰነበተ ምክር አለ፡፡
እንግዲህ ሰዎች ሲነከሱ ወደህክምና እንደሚሄዱ ቢገመትም፣ በውሻ ወይም በድመት ምላስ ቢላሱ ግን ቸግር የለውም ብለው ስለሚያምኑ ወደ ህክምና አይሄዱም፡፡ አደጋው ግን በመላስ ብቻ በባክቴሪያው ሊለከፉ ይችላሉ፡፡ ማስታወስ ያለብን እነዚህ አደጋ ላይ የሚወድቁ ሰዎች፣ በቁስልም ይሁን በአደጋ ሰውነታቸው ተላልጦ ክፍተት ስለሚኖራቸው ነው ባክቴሪያው በቀላሉ ወደ ሰውነት ውስጥ የሚዘልቀው፡፡ የውሻና የድመት አክቲቪስቶች ካሉ በጠላትነት እንዳይፈርጁኝ፣ በመረጃ የተመረኮዘ ዘገባ ነው ያቀረብኩት፣ የማገኘውም ጥቅምም የለም፡፡ የመረጃው ምንጭ የሚከተለው ነው፡፡ መልካም ንባባ አካፍሉ፡፡ የሰው ህይወት ልታድኑ ትችላላችሁ፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ግኝት ለሀኪሞችም አዲስ ሰለሆነ በማንበብዎ ከሀኪምዎ ቀደሙ ማለት ነው፡፡
Kannangara DW, et al. 79 cases of pet associated Pasteurella multocida infections in a 30-month period with reports of novel modes of non-bite transmission and their significance; Presented at: ASM Microbe; June 20-24, 2019; San Francisco
ሆስፒታሎች እኮ ንፁሕ አይደሉም!
ከሰሞኑ ከተለቀቁት ዜናዎች አንዱ፣ በሰኔ 16 በተደረገው የቦምብ ጥቃት የተጎዳ ወጣት ሆስፒታል ውስጥ እስከመጨረሻው እርዳታ ሳይደረግለት ወደቤቱ ተመለሰ የሚል ወቀሳ በጋዜጠኛ በኩል ቀረበ የሚል ነው፡፡ ጋዜጠኛው ጣቱን የቀሰረው ወደ ጠሚና አስተዳደራቸው ላይ ነው፡፡ እንደኔ፣ ጋዜጠኛው መጀመሪያ መጠየቅ የነበረበት፣ ጉዳተኛውን ያከሙና ያሰናበቱት ሀኪሞቸን ነበር፡፡ ምክንያቱን ሀኪም እንጂ ፖለቲከኞቹ ሊያውቁትም አይችሉም፡፡ ለነገሩ በኢትዮጵያ የማይደረግ የለም፡፡ ከዚህ በተያያዘ ግን አጋጣሚውን በመጠቀም ሰለ ሆስፒታሎችና ሆሰፒታል በመቆየት ብዛት ህሙማኑ ስለሚሸምቷቸው አስቸጋሪ በሽታዎች መግለፁ ጠቃሚ ሆነ አግኝቸዋለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መረጃ ባይኖረኝም፣ በአሜሪካ በጣም ትልቅ ችግር ስለሆነው በእንግሊዝኛ Hospital Acquired Infection (HAI) ተብሎ ስለሚጠራው ሁኔታ ነው፡፡ ህሙማን ለሌላ ህክምና ገብተው ሲረዱ በሆስፒታል ቆይታቸው ሰለሚይዛቸው ተጨማሪ ልክፍት ነው፡፡ በእንግሊዝኛው ምህፃረ ቃል HAI በሚለው እንቀጥል፡፡
መረጃው የሚያሳየው ከ25 ታካሚ አንዱ ይህ HAI እንደሚይዘው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተለያዩ ችግሮች ከመፍጠሩ በላይ ለህይወት ማለፍም ከፍተኛ ምክንያት ነው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ፣ ህሙማኑ የመሻል ምልክት እንዳሳዩ በፍጥነት ከሆስፒታል እንዲወጡ ተደርጎ፣ ረዥሙን ማገገሚያ ጊዜያቸውን በቤታቸው እንዲያደርጉ የሚደረገው፡፡
ይህ እንግዲህ ንፅህናቸው በከፍተኛ ደረጃ ይጠበቃል በሚባሉ በአሜሪካ ሆስፒታሎች ነው፡፡
በዚህ HAI የሚከሰቱ በሽታዎች ከመግለፄ በፊት ምክንያቱን ልግለፅ፤ ወደ ሆሰፒታሎች የሚዘልቁ ህሙማን በተለይም በተለያየ (ኢንፌክሽን) ልክፍት ምክንያት ሆስፒታል በሚቆዩበት ጊዜ፣ ከሕክምና ባለሙያተኞች ጋር በሚደረግ ንክኪ፣ በሆሰፒታል መገልገያ መሣሪያዎችና ዕቃዎች ላይ ልክፈቱን ያመጣው ባክቴሪያ፣ ፈንገስ ወይመ ቫይረስ ወደኋላ በመቅረት፣ ምንም ንፅህና ቢደረግ፣ ሆስፒታል ውስጥ መሽጎ ይቀመጣል፡፡ ሰለዚህ ይህ የተደበቀ ነገር ደግሞ ሌላው በሽተኛ ላይ በቀላሉ ኢንፌክሽን ይፈጥራል፡፡ ልብ በሉ፣ ይህ ህሙም ሲገባ ይህ ኢንፌክሽን አልነበረውም፡፡ እንግዲህ ሆስፒታል ውስጥ ስታዩ፣ ከጓንት ጀምሮ፣ የማጠቢያ ኬሚካሎች ሳሙናን ጨምሮ፣ ወይም በየክፍሉ ግድግዳ ላይ የምታዩት የእጅ ማፅጃ አልኮሆሎች ይህንን HAI ለመቀነስ የምንጠቀምባቸው ናቸው፡፡ ያም ተደርጎ ሁኔታውን መቆጣጠር አልተቻለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው ህዋስ በአብዛኛው ብዛት ያላቸው መድሐኒቶችን (ፀረ ህዋስ) የተለማመደ በመሆኑ እንዲሁ በቀላሉ መታከም የማይችል ነው፡፡ በእንግሊዝኛ Resistance የሚባለው ሁኔታ የተሸከሙ ህዋሳት ናቸው፡፡ በተለይም በነዚህ Resistance ባላቸው ህዋሳት መለከፍ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ህሙማን በአስቸኩዋይ ከሆስፒታል እንዲወጡ የሚደረገው፡፡ ዘመዴ ሆስፒታል ይክረምልኝ ማለት፣ በነዚህ ልክፍቶች ምክንያት የህይወት ማለፍ ስለሚያስከትል፣ በዚያው ሸኙልኝ ከማለትም ይቆጠራል፡፡
ለመሆኑ ምን አይነት በሽታዎች ናቸው በብዛት የሚታዩት፤
እኤአ በ2014፣ 75 ሺ ሰዎች በዚህ ሰበብ ህይወታቸው አንዳለፈ (በሰሜን አሜረካ) ይታወቃል፡፡ ይህ እንግዲህ ለሌላ ጉዳይ ገብተው ነው፡፡ CDC
ይህ ጉዳይ ትልቅ ሰለሆነ በየሆስፒታሉ infection control በሚል ፕሮገራም፣ ባለሙያተኞች ቀን ከሌት ይሠራሉ፡፡ ዋናው ነገር፣ ራሳቸው የህክምና ባለሙያተኞች ከአንድ በሽተኛ ወደ ሌላው ጀርሞችን ይዘው አንዳይሄዱ ንፅህና እንዲያደርጉ ይገደዳሉ፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን ወደቤታቸውም ይዘው እንዳይሄዱም ነው፡፡ የህክምና መገልገያ መሣሪያዎች መፅዳት የሚገባቸው፣ በሚፈቀደው የኬሚካል አይነት እንዲፀዱ፣ የሆስፒታል አልጋ፣ ግድግዳና ወለል ሳየቀር በአግባቡ በተፈቀደው ኬሚካል እንዲፀዱ ይደረጋል፡፡ ከዚህ ውጭ disposable የሚባሉ ለአንድ ህሙም ወይም ለአንድ አገልግሎት ከተጠቀምና በኋላ የምንጥላቸው እንደ መርፌ፣ ምላጭ፣ ጓንት የመሳሰሉትን ይጨምራል፡፡ የነዚህ ተጠቅሞ የሚጣሉ ዕቃዎች ይህንን HAI ለማስቀረት ነው፡፡
ለትዝብት ያህል እጁን ሳይታጠብ ወይም ሳትታጠብ ልምርምር የሚል ሀኪም ወይም ነርስ ካለ…..
የኛ ሀገር ሰው ህሙማን መጠየቅ ስለሚወድ፣ ሆስፒታሎች እስኪያማርሩ ድረስ ቦታ ሲያጣብብ ይታያል፡፡ እንግዲህ ሆሰፒታል ከሄዱ እጅዎን ታጥበው መውጣት፣ ከተቻለ በአልኮል እጅውን መወልወል ጥሩ ነው፡፡ ወደቤቱ የተመለሰ ህመምተኛ ካለ፣ ሆስፒታል የለበሰውን ልብስ ቶሎ አስውለቆ ማጠብ፡፡ የተገለገለበትን ዕቃም በእግባቡ ማሰወገድ ይረዳል፡፡ ይህን አካፍሉ ባካችሁ፡፡ 09/11/2018