​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

​ዕድሜ በገፉ ሰዎች የሰውነት እንቅስቃሴ መጨመር የኩላሊት በሽታን ከመባባስ ይቀንሳል


ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ከሚከተሉት የጤና ቀውሶች አንዱ የኩላሊት በሽታ ነው፡፡ ይህንን የኩላሊት በሽታ ከፋ ደረጃ እንዳይሻገር የሚደረጉ ነገሮች አሉ፡፡ በአብዛኛው፣ አስካሁን ድረስ የሚደረገው፣ ለኩላሊት በሽታ ጠንቅ የሆኑትን የደም ግፊትና የሰኳር በሽታን በመድሀኒት አማካኝነት መቆጣጠር ነው፡፡ ይህ ግን በራሱ፣ እነዚህ በዕደሜ የገፉ ሰዎችን ከሚገባው በላይ ብዛት ያላቸው መድሐኒቶች እንዲወስዱ፣ አንዳንዴም በመድሐኒቶች ምክንያት ጉዳቶች አንዲከሰቱ ነው ያደረገው፡፡ ጥያቄው ታዲያ፣ መድሐኒት ከመስጠት ውጭ ሌላ ምን አይነት ፕሮገራም፣ የኩላሊት በሸታን ወደከፋ ደረጃ ከመድረስ የሚቀነስ ነገር አለ ወይ ነው፡፡

ጃማ በሚባል የህክምና መፅሄት በቅርቡ የወጣ የምርምር ወይም የጥናት ውጤት ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሠጣል፡፡ እኔም የዘገየሁትን ያህል ይህን የጥናት ውጤት ስመለከት፣ በጉጉት ለህብረተሰቡ ለማካፈል ይህን ፅሁፍ አቅርቤያለሁ፡፡ መነበብ ይገባዋል የሚል እምነትም አለኝ፡፡

ሰለኩላሊት በሽታ በጥቂቱ ለመግለፅ፣ ዕድሜያቸው ከ70 አመታት በላይ በሆኑ ሰዎች ከአንድ ሶስተኛ በላይ በሆኑት የኩላሊት በሽታ ይገኝባቸዋል ወይም የታይባቸዋል፡፡ ይህ ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታው ሲለካ የኩላሊት የማጣራት ችሎታው ከ60 በታች ነው፡፡ ጤናማው ቁጥር አንግዲህ ነው፡፡ ችግሩ ምንድን ነው፡፡ የኩላሊት በሸታ ለብዙ በሽታዎች መከሰት ሰበብ ወይም ምክንያት መሆኑ ነው፡፡ በመጠኑ በዝርዝር ለማየት፣ የኩላሊት በሽታ የሚሰከትላቸው ጉዳቶችየሚከተሉት ናቸው፤ የልብና የደም ሥር በሸታዎች፣ የሰውነት አቅም መድከም፣ መውደቅ፣ ተከትሎ ስብራቶች፣ የአእምሮ የማሰብ ወይም የአውቀት ችሎታ መቀነስ፣ በህመም ምክንያት ወደ ሆሰፒታል መግባትና፣ ከዛም ለህይወት ማለፍ ምክንያት መሆን ነው፡፡ ባጠቃላይ ለከባድ ህመምና ለሞት ይዳርጋል፡፡

በቀረበው ጥናት፣ መጠነኛ የሰውነት እንቅስቃሴና የአካል አንቅስቃሴ ማድረግ ጤንነት ላይ የሚያሰከትለውን ውጤት ግምገማ ነው የምንመለከተው፡፡ ጥናቱ ያተኮረው ዕድሜያቸው ከ70 እሰክ 89 በሆኑ ሰዎች ሲሆን፣ አነዚህ ሰዎች፣ ወንድም ሆነ ሴቶች በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ የማያደርጉ ማለትም በቀን ከሀያ ደቂቃ በታች ወይም በሳምንት ከ125 ደቂቃዎች በታች የሰውነት ወይም የአካል እንቅስቃሴ የሚያደረጉ ባጠቃላይ መቀመጥ የሚያዘወትሩ ሰዎች ሲሆኑ በተጨማሪም፣ ለሰውነት መድከምና የዕለት ከለት ሥራ ወይም የኑሮ እንቅስቃሴ ማድረግ ሊሳናቸው የሚችሉና ሌሎችም መመዘኛዎችን ጨምሮ የጥናቱ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ተደረገ፡፡

እነዚህ ሰዎች ከሀለት ወገን ተከፍለው አንደኛው ወገን በተዘጋጀው የሰውነት እንቅስቃሴ ፕሮገራም ታሳተፊ ያልሆኑ ሲሆን፣ ሌሎቹ ግን በሚከተለው መንገድ የሰውነት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ተደርጎ ክትትል በማድረግ ውጤቱን ለመገምገም ነው፡፡ ፕሮገራሙ ሁለት አይነት ሲሆን፣ የመጀመሪያው ጠቅላላ የሰውነት እንቅስቃሴ ግቡም በየቀኑ በመራመድ ባጠቃላይ በሳምንት ውስት የ150 ደቂቃዎች መራመድ፣ ማለትም በየቀኑ ለ30 ደቂቃዎች መራመድ ነው፡፡ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ፣ የሰውነት ጥንካሬ፣ የሰውነት ሚዛን መጠበቅና የሰውነት መተጣጠፍ ለመጨመር የሚደረግ የአካል እንቅስቃሴ አንዲለማመዱና ቀጥሎም እንዲያዘወትሩ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህኛውም ቀስ ብሎ በመጀመር ግቡ፣ በቀን የአስር ደቂቃዎች ከወገብ በታች የሰውነት ክፍልን የሚያጠነክሩ እና ለአስር ደቂቃዎች የሰውነት ሚዛን መጠበቅ የሚያስችሉ እንቀስቃሴዎችን ማድረግ ነው፡፡ ሰዎቹ የሚጠበቅባቸው በየቀኑ ርምጃዎችና ቀደም ብለው የተጠቀሱትን የአካል አንቅስቃሴዎች በጥምር እንዲያደርጉ ነው፡፡  

ክትትሉ ሰዎቹ የሚያደርጉትን የሰውነትና የአካል እንቅስቃሴ መለካት በሚቻልበት ሁኔታ ፕሮገራሙ ሲጀመር ከዚያም በ12ኘው ወር፣ በ24ኘው ወይም በሁለት አመት መረጃዎችን በመሰብሰብ የታየውን ውጤት በስሌት ማየት ነው፡፡ እነዚህ መረጃዎች ሲበሰቡ በተጓዳኛም የኩላሊት የማጣረት ቸሎታን አብሮ ተለክቷል፡፡

ዝርዝር የጥናቱን አሰራር ወይም የተጠቀሙትን ዘዴ አልፍን ውጤቱ ላይ ስናተኩር፤ ከጠቅላለው 1635 የጥናቱ ተሳታፊዎቸ 1199 የሚሆኑት የኩላሊት ማጣራት ችሎታን ለማጥናት ናሙናዎች ሠጥተዋል፡፡ ከነዚህ መሀል አማካይ ዕድሜ 78.9 አመት ሲሆን፣ 66.7% ሴቶች ናቸው፡፡ ጥናቱ ሲጀመር የኩላሊት በሽታ እንዲባባስ ሊያደርጉ የሚችሉ ጠንቆች የስኳር በሽታ በ27.3% ሰዎች፣ የደም ግፊት በ855 ሰዎች፣ የልብና የደም ሥር በሽታ በ354 ሰዎች የነበራቸው ሲሆን፣ ሲጀመር የኩላሊት የማጣራት ችሎታው መጠን ከ60 በታች በ796 ሰዎች ላይ የታየ ነው፡፡

 የጥናቱን ውጤት ቁጥር በዝርዝር ሳናስቀምጥ የታየው ውጤት፣ የሰውነት እንቅስቃሴና የአካል እንቅስቀሴ እንዲያደርጉ በተመደቡት ወገን፣ ከሌሎች ጋር ሲወዳደር እየከፋ የሚሄደው የኩላሊት የመድከም ሁኔታ ያዘገመ ወይም የቀነሰ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡  የጥናቱ ባለቤቶች ደግመው የሚገልፁት ነገር፣ የአካል አንቅስቃሴ በሚያደርጉት ሰዎች፣ የእንቅስቃሴው መጠን በጨመረ ቁጥር፣ በየጊዜው የሚከሰተው የኩላሊት የመድከም ሁኔታ በጣም ያዘገመ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ማለትም የከፋ የኩላሊት በሽታ በፍጥነት ከመከሰት መከላከል ተችሏል፡፡

በማጠቃለያቸው የሚነግሩን ነገር፤ በጥናቱ በታየው ውጤት መሠረት፣ የሰውነት እንቅስቃሴ መጠነኛም ቢሆን የኩላሊት የከፋ ሁኔታ ደረጃን መድረስ የማዘግየት ጥቅም ሰላለው፣ የሰውነትና የአካል እንቅስቃሴ እንደመደበኛ ህክምና ለሰዎች መታዘዝ  እንዲኖርበት ነው የሚመክሩት፡፡

እንግዲህ እንዲህ አይነት ከመድሐኒት ውጭ በተፈጥሮ የሰውነት እንቅስቃሴ የኩላሊት በሸታን ማዘግየት ከተቻለ፣ በዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ወይመ የቤተሰብ አባላትን፣ በየቀኑ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ፣ ማለትም በቀን ለ30 ደቂቃዎች በአካባቢያቸው እንዲራመዱ፣ በተጨማሪም የታችኛው የሰውነት ክፍልን፣ እግርና ጭን የሚያጠነክር፣ ሚዛን መጠበቅ የሚያስችል የአካል እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ማበረታት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጥናት ጋር ያልተያያዘ በተለየም ርምጃዎች በሚያደርጉበት ጊዜ ፈጠን ያሉ ርምጃዎች ማድረግ የጠቅላላ የሰውነት ጥንካሬን እንደሚጨምሩ ቢታወቅም ይሀንን ጠቀሚታ ሁሉም ሰው ይገነዘባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ማስተዋል ያለብን ነገር ግን፣ ወደተፈለገው ግብ ለመድረስ ቀስ በቀስ እንዲሆን አንጂ ባንድ ጊዜ የታሰበውን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ከመገፋፋት መቆጠብ እንዳለብን ነው፡፡

መልካም ንባብ፡፡