ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ
Community health
education in Amharic
ታይፎይድ ሜሪ
ሰለ ታይፎይድ ፊቨር ካነሳን ስለ ታይፎይድ ሜሪ ትንሽ ፅሁፍ ማቅረብ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ የሴትዮዋን ታሪክ መጥቀስ አስፈላጊ የሆነው፣ በበሽታው ተይዘው ካገገሙ በኋላ ባክቴሪያው ከሰውነታቸው ሳይጠራ ቀርቶ፣ ለበሽታው መተላለፍ ምክንያት የሚሆኑ ጤናማ ተሸካሚዎች የሚባሉ ሰዎች እንዳሉ ለማስገንዘብ ነው፡፡ ይህ በሽታ፣ የግለሰብ ብቻ ሳይሆን የህብረተሰብ ችግር መሆኑን ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ታሪኩ እንደዚህ ነው
እኤአ 1907 በአሜሪካ የህብረተሰብ የጤና ታሪክ በስመ ጥፉነት የምትታወቅ ሜሪ ማሎነ ነገር ግን ታይፎይድ ሜሪ በመባል የምትጠራ ሴት በዘመኑ በኒው ዮርክ ከተማ ምግብ አብሳይ ነበረች፡፡ ታሪኩ የሚጀምረው፣ ሎነግ አይላንድ በተባለ የሀብታሞች የበጋ ማረፊያ ቤቶች ያልተጠበቀ የታይፎይድ ወረርሽኝ ሲከሰት ነው፡፡ ያልተጠበቀ ያደረገው ምክንያት፣ ይህ በሽታ የሚከሰተው ንፅህና በጎደላቸው የደሆች መንደሮች ስለነበር ነው፡፡ ሁኔታው ግራ ያጋባው የማረፊያ ቤቶቹ ባለንብረት ኢንጂነር በመቅጠር በሽታው ከየት እንደተነሳ ኢንዲያጣራለት ይጠይቃል፡፡ የተቀጠረው ኢንጂነር፣ የመጠጥ ውሃውና፣ በአካባቢው የነበረውን የአሳ መሸጫ ሱቅ ለበሽታው መሠራጨት ምክንያት አለመሆናቸውን ያረጋግጣል፡፡ ነገር ግን ክትትሉን በቤቱ ውስጥ በምግብ አብሳይነት ተቀጥራ በምትሠራው ሜሪ ማሎን በምትባል ሴት ላይ ያተኩራል፡፡ ወረርሽኙ የተከሰተው ሴትዮዋ በተቀጠረችበት አካባቢ ነበር፡፡ ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ ግን ሴትዮዋ ሥራዋን ለቃ ሄዳለች፡፡ ኢንጂነሩም ስለ ሴትዮዋ የሥራ ቅጥር ሲያጣራ፣ ሴትዮዋ በተቀጠረችበት ቦታ ሁሉ የታይፎየድ ወረረሽኝ የተከሰተ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ሴትዮዋን እንደ ምንም ፈልጎ ያገኛትና እንድትመረመር በሚጠይቃት ወቅት በእጇ በያዘችው ሹካ ከማስፈራራት ውጭ በፍፁም ፈቃደኛ አልሆነችም፡፡ የከተማው የጤና ቢሮ ሠራተኛ የሆኑት ሀኪም ከአምስት ፖሊሶች ጋራ በመሆን፣ ሴትዮዋ እንድትያዝ ተደርጎ የሠገራ ምርመራ ይደረግላታል፡፡ እንደ ተጠረጠረው፣ በሴትዮዋ አይነ ምድር ታይፎይድ ፊቨር የሚያመጣው ባክቴሪያ ይገኝባታል፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ሴትዮዋ በሽታውን እንዳታዛምት ተከልላ ለብቻዋ ከሌሎች ሰዎች ጋር በማትገናኝበት ሁኔታ እንድትኖር ይደረጋል፡፡
አንግዲህ ይች ሴትዮ ጤነኛ ተሸካሚ ከሚባሉ ነገር ግን ባከቴሪያውን በሰውነታቸው ይዘው በአይነ ምድር ንክኪ አማካኝነት ወደ ሌሎች ሰዎች እንዲተላለፍ ከሚያደርጉ ሰዎች አንዷ መሆኗ ነው፡፡ የጤና ቢሮው ተደጋጋሚ ምርመራ በሚያደርግበት ወቅት፣ ባክቴሪያው በሴትዮዋ አይነ ምድር ውስጥ በመገኘቱ፣ ለአራት አመታት በግዞት መልክ ለብቻዋ እንድትኖር ይደረጋል፡፡ በኋላ ግን፣ የጤና ቢሮው ሀላፊዎች፣ ሴትዮዋ በምግብና በመጠጥ ቦታ እንዳትሠራ ቃል አስገብተው፣ በተጨማሪም በየጊዜው በጤና ቢሮው እየመጣች ሪፖርት እንድታደርግ ተስማምታ ትለቀቅና ነፃነቷን ታገኛለች፡፡ በመንግሥት ትዛዝ በግድ አንድ ቦታ ተወስና እንድትኖር በመደረጉ፣ ሜሪ ማሎን የብዙ ሰዎችን ርህራሄ አግኝታ ሰለነበር በመለቀቋ የተደሰቱ ሰዎች ነበሩ፡፡
ታሪኩ በዚህ አላቆመም፡፡ ሴትዮዋ ከተለቀቀች ከአምስት አመታት በኋላ፣ በአንድ ሆስፒታል ውስጥ የታይፎይድ ወረረሽኝ ይከሰታል፡፡ ሁኔታው ሲጣራ፣ በቅርብ ጊዜ የተቀጠረች የሆስፒታሉ የምግብ አብሳይ የሆነች ወይዘሮ ብራውን የተባለች ሴት የባክቴሪያው ምንጭ ሆና ትገኛለች፡፡ ወይዘሮ ብራውን ደግሞ ሌላ ሰው ሳትሆን፣ ያችው ሜሪ ማሎን ስሟን ቀይራ በመቀጠሯ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የሚያዝንላት ሰው ልታገኝ አልቻለችም፡፡
አሁንም ተይዛ ለብቻው ወደምትኖርበት ቦታ ተልካ ህይወቷ እሰከሚያልፍ ድረስ በዚህ ቦታ እንድትኖር ትደረጋለች፡፡ በመሀሉ ግን በሆስፒታል ውስጥ በረዳትነት ስትሰራ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ህይወቷ ካለፈ በኋላ ግን ታይፎይድ ሜሪ የሚባለው መጠሪያ እንደቀጠለ ነው፡፡ በጤና መስክ የተሠማሩ ሠዎች ይህንን ስም በሚገባ ያውቃሉ፡፡ አሁን ደግሞ እርስዎ እንዲያውቁ አድርገናል፡፡ በዘመኑ የነበሩ ጋዜጦች፣ ሴትዮዋን የምትራመድ የታይፎይድ ፋብሪካ የሚል ስም ሰጥተዋት ነበር፡፡
ዋናው መልክት በበሽታው እንዳይያዙ አስፈላጊ ጥንቃቄ ማድረግ ሲሆን፤ ድንገት ተይዘው ካገገሙ በኋላ ደግሞ ባክቴሪያው ከሰውነትዎ መጥራቱን ለማረጋገጥ ተከታታይ የአይነ ምድር (ሠገራ) ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ በምግብ አካባቢ የሚሠሩ ከሆነ፣ ለሌሎች ቤተሰብን ጨምሮ ምግብ የሚያዘጋጁ ከሆነ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ባክቴሪያው ካልጠራ የሰው ምግብ ባይነካኩ ይመከራል፡፡ እንግዲህ ንፅህና ወሳኝ የሚሆነው እዚህ ላይ ነው፡፡ በሽታው በአይነ ምድር ንክኪ ስለሚተላለፍ፣ የመፀዳጃ ቤቶች መኖር፣ እጅን በበቂ ውሀ መታጠብ አስፈላጊ ስለሆነ፣ በቂ የውሀ አቅርቦት መኖር ወሳኝ ነው፡፡ ለራስዎ፣ ለቤተሰብዎ ሆነ ለህብረተሰቡ ሲሉ ማስተማርና መምከር፣ የአካባቢን ንፅህና በጋራ መጠበቅ ጠቃሚ ነው፡፡ በመንገድ ዳር ያለ አይነ ምድር ለአፍንጫ ከሚሠጠው ጠረን በላይ ሌላ ጉዳትም ያስከትላል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው ታሪክ እንዳየነው፣ በአካባቢያችን እንደታይፎይ ሜሪ ሁሉ፣ ታይፎይድ በለጠ፣ ታይፎይድ ከበደ፣ ወይም ታይፎይድ ዘውድነሽ፣ ታይፎይድ ወድነሽ ባይኖሩ ምኞታችን ነው፡፡ ልብ በሉ እነዚህ ጤናማ ተሸካሚ የሚባሉ ሰዎች፣ ባክቴሪያውን በሰውነታቸው ሲሸከሙ ምንም የህመም ስሜት እንደማይኖራቸው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ምርመራ ካልተደረገ በቀር ሊታወቅ አይችልም፡፡ ሰለዚህ በሚኖሩበት አካባቢ ምግብ የሚያዘጋጁ ሠራተኞች በቂ የጤና ምርመራ ይደረግላቸው ይሆን? አስኪ ያጣሩ፡፡ለሌሎች አካፍሉ