​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

የስኳር ህመም በዓይን ላይ የሚያስከትለዉ ችግር
(በፕ/ር የሺጌታ ገላዉ)


የስኳር ህመም ሰዉነታችን ለእለት ከለት እንቅስቃሴና እድገት የሚያስፈልገዉን የስኳር መጠን በትክክልና በተገቢዉ መንገድ መጠቀም ሳይችል ሲቀር የሚመጣ አጠቃላይ የጤና ችግር ነዉ። ይህ የሚሆነዉ ደግሞ በዋናነት ቆሽት (ፓንክሪስ) የተባለዉ የሰዉነት ክፍል ሰዉነታችን ስኳርን በአግባቡ ለማሰራጨትና ለመጠቀም የሚረዳዉን ‹‹ ኢንሱሊን ›› የሚባል ፈሻሽ ንጥረ ቅመም በሚፈለገዉ መጠን ሳያመነጭ ሲቀር ወይም የማመንጨት ሥራዉን ከናካቴዉ ሲያቆም ነዉ።
ይህም ችግር በደማችን ዉሥጥ የሚገኘዉ የስኳር መጠን ከሚገባዉ በላይ ከፍ እንዲልና በተለያዩ የሰዉነት ክፍሎች ላይ (ለምሳሌ ዓይን፣ ኩላሊት፣ ልብ፣ ነርቭ፣ የደም ሥር፣ ወዘተ) ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ ዓይነ ስዉርነት፣ ከባድ የኩላሊት ህመምና ሥራ ማቆም፣ ድንገተኛ የልብ ህመም፣ የጭንቅላት ደም መፍሰስ፣ የእግር መቆረጥና ሌሎች ከባድ ችግሮችን ያስከትላል።

በዋናነት ሁለት አይነት የስኳር ህመሞች ሲኖሩ ‹‹የመጀመሪያ አይነት የስኳር ህመም›› (ከ30 ዓመት የእድሜ ክልል በታች የሚከሰተዉ) እና ‹‹የሁለተኛዉ አይነት የስኳር ህመም›› (በብዛት ከ40 ዓመት የእድሜ ክልል በላይ የሚከሰተዉ) በመባል ይጠራሉ። ከ10-15 በመቶ (10-15%) የሚሆኑት የስኳር ህሙማን የመጀመሪያዉ አይነት የስኳር ህመም ሲኖርባቸዉ የተቀሩት ከ85-90 በመቶ (85-90%) የሚሆኑት ደግሞ የሁለተኛዉ አይነት የስኳር ህመም ተጠቂዎች ናቸዉ።

የስኳር ህመም ባሁኑ ሰዓት እጅግ በከፍተኛ ፍጥነት በወረርሽኝ መልክ እየተስፋፋ ያለ የጤና ችግር ነዉ። ባለፉት ዓመታት ያደጉ አገሮች ዋና የጤና ችግር ሆኖ የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ባለዉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለዉጥ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊና በመልማት ላይ ባሉ ሀገሮች አሳሳቢና ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ተላላፊ ያልሆነ የስኳር ህመም በዓይን ላይ የሚያስከትለዉ ችግር የጤና ችግር ከሆነ ዉሎ አድሯል። አለም ዓቀፉ የስኳር ህመም ፌደሬሽን በፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጥር በ2015 ዓ.ም ባወጣዉ መረጃ መሠረት ባሁኑ ሰዓት በአማካይ 415 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የስኳር ህመም ሲኖርባቸዉ የተቀናጀ፣ የተደራጀና አመርቂ የሆነ የመከላከልና የመቆጣጠር እርምጃ ካልተወሰደ የታማሚዎች ቁጥር በ2040 ዓ.ም ወደ 642 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል አሳዉቋል። ይህም ማለት ከዐሥር አዋቂ ሰዎች አንዱ የስኳር ህመም ተጠቂ ይሆናል ማለት ነዉ።

የስኳር ህመም በተለያዩ የሰዉነት ክፍሎች ላይ በሚገኙ የደም ስሮች፣ ነርቮችና ፈሳሽ አመንጭ የተፈጥሮ ዕጢወች ላይ ጉዳት ከማድረሱም በላይ አጠቃላይ በሽታ የመቋቋም አቅምን ያዳክማል። ዓይናችንም የራሱ የሆኑ የደም ሥሮች፣ ነርቮች፣ ፈሳሽ አመንጭ የተፈጥሮ ዕጢወች፣ በሽታ ለመቋቋም የሚረዱ ህዋሳትና ሌሎች ተፈጥሯዊ የበሽታ መከላከያ መሣሪያዎች አሉት። የስኳር ህመምም በእነዚህ ለዓይን ሕልዉና አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ጉዳት በማድረስ በዓይን ላይ የተለያዩ ችግሮች እንዲከሰቱ ያደርጋል።

በዋናነት የምንመለከተዉ የስኳር ህመም በብርሃን መቀበያ ክፍል (ረቲና) ላይ የሚያመጣዉን የጤና መታወክ ቢሆንም የስኳር ህመም በዓይን ላይ የሚያመጣዉን አጠቃላይ ተጽዕኖ መገንዘብ እንዲቻል በብዛት የሚከሰቱ ዋና ዋና ችግሮችን ጠቅሼ አልፋለሁ።
1. የዓይን እንቅስቃሴ ሚዛን መዛባት፤
2. ተደጋጋሚ የዓይነ ቆብ ልክፈት /ምርቀዛ/፤
3. የዓይን ድርቀት፤
4. የዓይነ መስታወት ምርቀዛ /ቁስለት/፤
5. የዓይን ግፊት ህመም፤
6. የዓይን ሞራ ችግር፤
7. የረቲና የጤና መታወክ፤
8. የእይታይ ነርቭ ችግር፤
9. በስኳር መጠን ማነስ ወይም መብዛት የሚመጣ ጊዜያዊ የእይታ ብዥታ፤ ወዘተ፡፡

በስኳር ህመም የሚመጣ የረቲና ጤና መታወክ

በአጠቃላይ ሲታይ በስኳር ህመም የሚመጣ የረቲና ጤና መታወክ (በእንግሊዝኛዉ አጠራር ‹‹ ድያቤቲክ ረቲኖፓቲ ›› ) ከሦስት የስኳር ህመምተኞች አንዱን የሚያጠቃ ሲሆን ችግሩ ባደጉ (በሰለጠኑ) ሀገሮች በሚኖሩ የስኳር ህመምተኞች ላይ ዓይነ ስዉርነት ከሚያመጡ የተለያዩ መንስኤዎች አንዱና ዋነኛዉ ነዉ። አምስት በመቶ (5%) የሚሆነዉ በዓለማችን ላይ የሚከሰተዉ የዓይነ ስዉርነት ችግር የስኳር ህመም በሚያስከትለዉ የረቲና ጤና መታወክ ምክንያት የሚመጣ ሲሆን የችግሩ ስፋትና የጉዳቱ መጠን በታዳጊ ሀገሮች ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ እንደሚሄድ መረጃዎች ያሳያሉ። በሀገራችን ኢትዮጵያ ከሚኖሩ የስኳር ህመምተኞች ከ40 በመቶ (40%) ባላይ የሚሆኑት የረቲና የጤና መታወክ እንዳለባቸዉ ጥናቶች ያመለከቱ ሲሆን የዓይን ምርመራ በማድረግ ችግሩ እንዳለባቸዉ የሚያዉቁት ደግሞ እጅግ ጥቂቶች ብቻ ናቸዉ።

የከፋ የረቲና መታወክ ያለባቸዉ የስኳር ህመምተኞች ተያያዥ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና ስነልቦናዊ ችግር ስለሚገጥማቸዉ የእይታ ችግሩ በአጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤአቸዉ ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል። የዚህ ችግር መከሰት በቀጥታ ከስኳር ህመም የቆይታ ጊዜ ጋር የተቆራኘ ሲሆን ቁጥጥር ያልተደረገበት የደም ዉሥጥ የስኳር መጠን፣ የደም ግፊት እና የደም ዉሥጥ የቅባት መጠን ለችግሩ መከሰት አብይ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። የስኳር ህመም የቆይታ ጊዜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የረቲና ጤና መታወክ የመከሰት እድሉ እየጨመረ ይሄዳል።

ዓይናችን የሚያስፈልገዉን ምግብ፣ ንጥረ ነገርና አየር (ኦክስጂን) የሚያቀርብለት ደም ቅዳ እንዲሁም አገልግሎት ላይ የዋለና የተቃጠለ ተረፈ ምግብና ንጥረ ነገር የሚያስወግድበት ደም መልስ አለዉ። ዋናዎቹ የደም ሥሮች ማእከላዊ የረቲና ደም ቅዳና ደም መልስ በመባል ይጠራሉ። በተለያዩ የጤና ችግሮች (ለምሳሌ የስኳር ህመም፣ የደም ግፊት፣ የዓይን መመታት፣ ወዘተ) ምክንያት የሚደርስ የዓይን ጉዳት በእነዚህ ጥቃቅን የረቲና ደም ቅዳዎችና ደም መልሶች ላይ ጉዳት ያደርሳል። ጉዳቱም ከእነዚህ ጥቃቅን የረቲና የደም ሥሮች ደም እንዲፈስና ረቲናዉ ዉኃ መሰል ፈሳሽ እንዲቋጥር በማድረግ እንዲያብጥ ያደርጋል።

የደም መፍሰሱ እንዲሁም የተፈጠረዉ የረቲና እብጠት ከፍተኛ ከሆነ ወይም ዋና የማያ ክፍል የሆነዉና ሠገነተ እይታ (Macula) ተብሎ የሚጠራዉ የረቲና ማእከላዊ ክፍል ጉዳት ከደረሰበት የእይታችን መጠንና ጥራት ይቀንሳል።
በረቲና የደም ሥሮች ላይ የደረሰዉ ጉዳት እየጨመረ ከሄደና ዋና የችግሩ መንስዔ የሆኑትን የጤና እክሎች ማከምና መቆጣጠር ካልተቻለ ለዓይናችን የሚደርሰዉ የደምና የኦክስጂን መጠን በከፍተኛ ደረጃ ስለሚቀንስ ረቲና ተገቢዉንና የሚጠበቅበትን ሥራ ለማከናዎን የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠራል:: ይህም ከፍተኛ የረቲና የደም ዝዉውርና ስርጭት መዛባት ከማስከተሉም በላይ፡-
 ረቲና መደበኛ ቦታዉን እንዲለቅ፣
 ከፍተኛ መጠን ያለዉ ደም ዓይን ዉስጥ እንዲፈስና
 ከባድ የሠገነተ እይታ እብጠትና ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ ለከፋ የእይታ መቀነስ ወይም ዓይነ ስዉርነት ይዳርጋል::

በስኳር ህመም ለሚመጣ የረቲና ጤና መታወክ ህክምናዉ ምንድን ነዉ?

ለዚህ ዓይነት ችግር ከሚደረገዉ ወርሃዊ መደበኛ ምርመራና ክትትል ባሻገር ለደረሰዉ የዓይን ጉዳት ህክምና ማድረግ የግድ ሲሆን የሚደረገዉ ህክምና እንደ ችግሩ አይነትና የጉዳት ደረጃ፣ እንደ ታካሚዉ አጠቃላይ የጤና ሁኔታና ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች የሚለያይ ቢሆንም የሚከተሉት አራት የህክምና ዓይነቶች እይታ የበለጠ ሳይጎዳ ባለበት ለማቆየት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።



በጥቅሉ በስኳር ህመም ምክንያት የመጣ የረቲና ጤና መታወክ በህክምና የመዳን እድሉ ከፍተኛ ነዉ። ነገር ግን ህክምናዉ ዉጤታማ የሚሆነዉ ችግሩ ሳይበረታና እይታ ሳይጎዳ ከተደረገ ብቻ ነዉ። ይሁን እንጂ ብዙ ታካሚዎች በጣም ዘግይተዉ ስለሚመጡ ያላግባብ የዓይን ብርሃናቸዉን የሚያጡበት አጋጣሚ ይከሰታል።
አንድ ቤቱ በእሳት የተቃጠለበት ሰዉ የጎረቤት ሰዎች ወይንም የእሳት አደጋ ሠራተኞች ደርሰዉ ቃጠሎዉን እንዲያጠፉለትና ንብረቱን ከዉድመት እንዲታደጉለት ከፈለገ ለጎረቤት ወይም ለእሳት አደጋ ሠራተኞች የድረሱልኝ ጥሪዉን ቃጠሎዉ እንደጀመረ ማድረግ ይኖርበታል። ይህን ካላደረገ ወይም የድረሱልኝ ጥሪዉን ዘግይቶ ካሰማ ጎረቤት ቢሰበሰብ፣ የእሳት አደጋ ሠራተኛ ቢመጣ ቤቱንና ንብረቱን መታደግ አይቻልም። እሳቱን ማጥፋት ቢቻል እንኳ ከቃጠሎዉ የሚተርፈዉ የቤት ክፍል ወይም ንብረት ብዙ የማይጠቅም ይሆናል። የስኳር ህመም ያለበት ሰዉም የእይታ ለዉጥ ወይም መቀነስ እንዳየ ብዙ ቀናትን ወይም ሳምንታትን ሳይጠብቅ የዓይን ምርመራ ካላደረገ ዉጤታማ ህክምና አድርጎ እይታዉን የመታደግ እድሉ እጅግ እያነሰ ከመሄዱም በላይ ምንም አይነት የህክምና እርዳታ ወደማይሰጥበት የጉዳት ደረጃ ሊደርስ ይችላል።

ሀ . ጥብቅ የስኳር መጠን ቁጥጥርና ክትትል

ይህ ጥብቅ የስኳር መጠን ቁጥጥርና ክትትል በዉሥጥ ደዌ ወይም በስኳር ህመም ድህረ ስፔሻሊስት ሀኪሞች የሚከናወን ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከመጠን ያለፈ የደም ዉሥጥ የቅባት መጠንና ዉፍረት መቀነስ፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የደም ግፊትን መቆጣጠርና የኩላሊት ህመምን ባግባቡ መታከምና መከታተል ያስፈልጋል። እነዚህ ተዛማጅ የጤና ችግሮች በራሳቸዉ ከሚያመጡት የዓይን ጉዳት በተጨማሪ የስኳር ህመም በዓይን ላይ የሚያደርሰዉን ጉዳት እንዲባባስ በማድረግ ረገድ ጉልህ ድርሻ አላቸዉ። ስለሆነም አጋላጭ የሆኑ ችግሮችን ማስወገድና ተጓዳኝ የጤና ችግሮችን መታከምና መቆጣጠር የዓይን ህክምናዉን ዉጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ስላለዉ ህሙማን የስኳር መጠንን ከመቆጣጠር በተጨማሪ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ ነዉ።

ለ . የብርሃን ጨረር (የሌዘር ) ህክምና

ይህ ህክምና በረቲና ላይ የሚደርሰዉ ጉዳት እንዳይጨምር እንዲሁም ሌላ የከፋ ችግር እንዳይመጣና ጉዳቱ ባለበት እንዲቆም በማድረግ ዘለቄታዊ መፍትሄ ይሰጣል ። ይህ የሌዘር ህክምና በወቅቱ ከተደረገ በከፍተኛ የረቲና የደም ዝዉዉር መዛባት ምክንያት የሚመጣዉን ዓይነ ስዉርነት ከስድሳ እስከ ዘጠና በመቶ (60-90%) ይቀንሳል። እሳትን ለማጥፋት ዉኃ እንደምንጠቀም ሁሉ በስኳር ህመም ምክንያት የመጣን የረቲና መታወክ የሌዘር ህክምና በማድረግ ማስቆም ይቻላል። ይሁን እንጂ በዉኃ እሳትን ማጥፋት የተቃጠለ ንብረትን እንደማይመልስ /እንደማይታደግ/ ሁሉ የሌዘር ህክምናም የተጎዱ የረቲና ህዋሳትን ስለማይጠግን መሠረታዊ የሆነ የእይታ መሻሻል አያመጣም። የሌዘር ህክምና በራሱ መቶ በመቶ ዉጤታማ ስላይደለ ህክምናዉ ከተደረገ በኋላም ከፍተኛ የሆነ የረቲና ጉዳት ካለ የጉዳቱን ቀጣይነት ሙሉ ለሙሉ ማስቆም ስለማይቻል እይታዉ በተወሰነ ደረጃ መቀነሱ አይቀርም። ስለሆነም ጉዳቱ የከፋ ደረጃ ሳይደርስ የሌዘር ህክምናዉን ማድረግ ያስፈልጋል። ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንደሚባለዉ የሌዘር ህክምና መደረግ አለበት በሚባልበት ጊዜ ህሙማን ሳይፈሩና ሳይጨነቁ በወቅቱ ህክምናዉን ሊያደርጉ ይገባል። በግንዛቤ እጥረት ለዚህ ህክምና ተባባሪ ባለመሆን የዓይን ብርሃናቸዉን የሚያጡ ህሙማን ቁጥራቸዉ ቀላል አይደለም።

ሐ . የመድኃኒት ህክምና

በራሱ ፍጹም ዘለቄታዊ ፈዉስ የሚያመጣ መድኃኒት ለጊዜዉ ባይኖርም ከአጭር እስከ መካከለኛ ጊዜ በሠገነተ እይታ ላይ የተፈጠረዉን መድማትና ማበጥ በመቀነስ እይታን የሚያሻሽሉ አለያም ጉዳቱ እንዳይባባስ የሚያደርጉ ብዙ ዉጤታማ መድኃኒቶች አሉ። በእይታ አደባባይ ላይ ለሚፈጠር የመድማትና የማበጥ ችግር የመድኃኒት ህክምና ከሌዘር ህክምና ጋር ተመጣጣኝ ወይም ተቀራራቢ የሆነ ዉጤት አለዉ። እነዚህ ልዩ የዓይን መድኃኒቶች (ለምሳሌ ‹‹ሉሴንቲስ››፣ ‹‹አቫስቲን››፣ ‹‹አይሊያ››፣ ኮርቲዞን (ትራያምሲኖሎን የሚባል ስቴሮይድ)፣ ወዘተ) በመርፌ ዓይን ዉሥጥ የሚወጉ ሲሆን ከ3-6 ወር ለሚሆን ጊዜ ችግሩን ለመቆጣጠር ወይም ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። እንዳስፈላጊነቱ የተሻለ ዉጤት እስኪገኝ ድረስ እነዚህን መድኃኒቶች ደጋግሞ መወጋት ሊያስፈልግ ይችላል።

መ . የረቲና ቀዶ ህክምና

ይህ ህክምና ከፍተኛ የሆነ በሌዘርና በመድኃኒት መታከም የማይችል ችግር ላለባቸዉ ሰዎች የሚደረግ ሲሆን ልምድ ባላቸዉ የረቲና ቀዶ ጥገና ድህረ ስፔሻሊስት ሀኪሞች በከፍተኛ የህክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ይከናወናል። ይህ አይነት ቀዶ ህክምና እንዲደረግ ምክንያት የሚሆኑት ዋና ዋና ችግሮች የሚከተሉት ሲሆኑ ጉዳቱ ከፍተኛ ደረጃ ሳይደርስ ወቅታዊና ተገቢ የቀዶ ጥገና ህክምና ማድረግ ለህክምናዉ መሳካት የጎላ ድርሻ ስላለዉ ችግሩ ያለባቸዉ የስኳር ህሙማን ልብ ሊሉ ይገባል። ዋና ዋና ምክንያቶቹ፡-
1. ከፍተኛ የዓይን ዉሥጥ መድማትና የደም መከማቸት (የምልግልግ አካል በደም መሞላት)፣
2. የረቲና ከመደበኛ ቦታዉ መላቀቅ እና
3. የሰገነተ እይታ በማይፈለግ ስስ ልባስ መሸፈንና ያላግባብ መወጠር ናቸዉ።

በአጠቃላይ ከላይ የተገለጹት የስኳር ህመም ለሚያመጣዉ የረቲና የጤና መታወክ ( ‹‹ ዲያቤቲክ ረቲኖፓቲ ›› ) የሚደረጉ አራት የህክምና ዘዴዎች ሙሉና ዉጤታማ የሚሆኑት ታማሚዉ ስለህመሙ በቂ ግንዛቤ ሲኖረዉና ለሚደረገዉ ህክምና ንቁና በቂ ተሳትፎ ሲያደርግ ብቻ ነዉ። ይህ ካልሆነ ለስኳር ህመም የሚደረገዉ ህክምና በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ ይቆጠራል። በተለይ በታዳጊ ሀገር የሚኖሩ አብዛኛዉ ህሙማን ስለችግሩ ያላቸዉ ግንዛቤ አናሳና ግልብ ከመሆኑም በላይ ለህክምና የሚያስፈልገዉን ወጭ መሸፈን ስለማይችሉ ከሚኖረዉ የህክምና መድኃኒትና የመሣሪያ አቅርቦት እንዲሁም የረቲና ሀኪም እጥረት ጋር ተዳምሮ የስኳር ህመም በዓይን ላይ የሚያደርሰዉን ጉዳት መጠነ ሰፊና የከፋ ያደርገዋል። በስኳር ህመም የሚመጣ የረቲና መታወክ ባደጉ (በሰለጠኑ) ሀገሮች በሚኖሩ ሰዎች ላይም ሳይቀር ዓይነ ስዉርነት ከሚያመጡ ችግሮች አንዱና ዋነኛዉ ነዉ።

የስኳር ታማሚ የዓይኑን ጤና መጠበቅ የሚችለዉ እንዴት ነዉ?

1. የደም ዉሥጥ የስኳር መጠንን፣ የደም ግፊትንና የደም ዉሥጥ የቅባት መጠንን ከዉሥጥ ደዌ ስፔሻሊስትና የስኳር ሀኪሞች ጋር በመመካከር ባግባቡ መቆጣጠር። እንዲሁም የኩላሊት ህመምን ባግባቡ በመታከም የጉዳት መጠኑን መቀነስ።
2. መደበኛና ወቅታዊ የዓይን ምርመራ ልምድና ክህሎት ባለዉ የዓይን ህክምና ባለሙያ ማድረግ፡- ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ መታየት የግድ ይላል።
3. ለእይታ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት፡- አንድ ዓይንን ተራ በተራ በመጨፈንና በአንድ ዓይን ብቻ በማየት የሁለቱም ዓይኖች እይታ ጥሩ መሆኑን ማረጋገጥና የእይታ ለዉጥ ካለ ወዲያዉኑ የዓይን ምርመራ ማድረግ። ከእይታ መቀነስ በተጨማሪ በሚያነቡበት ጊዜ ቀጥ ያሉ መስመሮች ተወላግደዉ፣ ተጣመዉ ወይም ዝግዛግ ሠርተዉ እንዲሁም ፊደላት የተዛባ ቅርጽ ይዘዉ የሚታዩዎት ከሆነ በፍጥነት ሊታዩ ይገባል።
4. በሀኪም የሚሰጡ ምክሮችን መተግበርና የሚደረጉ ህክምናዎችን ባግባቡ መከታተል፤
5. በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ማዳበር
6. አልኮል የሚጠጡ ከሆነ የሚወስዱትን የአልኮል መጠን መቀነስ።
(የዓይን ጤናና ክብካቤ በፕ/ር የሺጌታ ገላዉ)