Health and History

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

ለኤች አይ ቪ ቫይረስ ቢጋለጡም በቫይረሱ የማይለከፉ ሰዎች እንዳሉ ያውቃሉ ወይ

ሰዎች በተፈጥሯቸው ለበሽታ የተለያየ ምላሽ እንዳላቸው ግልፅ ነው፡፡ ወደ ኤች አይ ቪ ከመሄዳችን በፊት ሌሎች ቫይረሶችን እንመልከት

ለምሳሌ የጉበት በሽታ በማሰከተል በአለም ዝነኛው ቫይረስ ሔፓታይትሰ ቢ ነው(Hepatitis B)፡፡ ሰዎች ለዚህ ቫይረስ በሚጋለጡበት ጊዜ ከመቶ ሰማንያ አምሰት (85%) የሚሆኑት ሰዎች ቫይረሱን በተፈጥሮ መከላከያቸው ጠርገው በማውጣት በበሽታው ሳይለከፉ እንደሚቀሩ ይታወቃል፡፡

ሌላውን የጉበት በሽታ የሚያስከትለውን የሔፓታይትሰ ሲ ቫይረስ (Hepatitis C) ስንመለከት ለዚህ ቫይረስ ከተጋለጡ ሰዎች ከመቶ አስራአምስት (15%) የሚሆኑት ቫይረሱን ከሰውነታቸው ባላቸው የተፈጥሮ መከላከያ አማካኝነት ጠርገው በማውጣት በቫይረሱ ሳይለከፉ ይቀራሉ፡፡ የቀሩት 85% የሚሆኑት ግን ቫይረሱ በሰውነታቸው ውስጥ በመቅረት የጉበት በሽታ እና የጉበት ካንሰር ሊከሰትባቸው ይችላል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት ሔፓታይትስ ሲ ቫይረስን በህክምና ማዳን ከተቻለ ስንበት ብሏል፡፡ የዚህ ርዕስ ፀሐፊ ለዚህ በቂ ምስክር ነው፡፡ ብዛት ያላቸው ህሙማንን ከቫይረሱ በመፈወስ፡፡ ትልቁ ችግር መድሃኒቶቹ ውድ መሆናቸው ነው፡፡ አንደ ኪኒኒ (እንክብል) አንድ ሺ የአሜሪካ ዶላር በላይ ያወጣል፡፡ በአብዛኛው ህክምናው ለሶስት ወር ብቻ ስለሚሰጥ ስሌቱን ለአንባቢ እተዋለሁ፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ቫይረሶች የተጋለጡ ሰዎች በደም ምርምራ ለቫይረሱ ተጋልጠው እንደነበር ማወቅ ይቻላል፡፡ የዳኑትም ሆነ ቫይረሱን በሰውነታቸው ውስጥ ተሸክመው የቀሩት፡፡

እንግዲህ ወደ ኤች አይ ቪ ስንመለስ ለበሽታው ጨርሶ መጥፋት ሚስጥሩን የያዙት ስለሚባሉ ሰዎች ላካፍል፡፡ እነዚህ ሰዎች በተደጋጋሚ ለቫይረሱ ተጋልጠው ነገር ግን ባላቸው የተፈጥሮ መከላከያ ምክንያት በቫይረሱ ሳይለከፉ የሚቀሩ ናቸው፡፡ በእንግሊዝኛው አጠራር Highly Exposed Sero Negatives ይባላሉ፡፡ ለዚህም በቂ ጥናት ተደርጓል፡፡ በአፍሪቃ ውስጥ ሴትኛ አዳሪዎቸን በመከታተል በተደረገው ጥናት ሴቶቹ ያለምንም መከላከያ ግብረ ሥጋ ግንኙነት በተደጋጋሚ ቢያደርጉም ሌሎች እኩዮቻቸው በቫይረሱ ሲለከፉ እነሱ ግን ሳይያዙ ቀርተዋል፡፡ በጣም የሚያስገርም ሁኔታ ነው፡፡ በአሜሪካም በግብረ መሰል ፆታ ግንኙነት ያለምንም መከላከያ ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች ጓደኞቻቸው ሲለከፉ እነሱ ሳይለከፉ ቀርተዋል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት የጉበት ቫይረሶች ሁኔታ የሚለየው እነዚህ በኤች አይ ቪ ቫይረስ ያልተለከፉ ሰዎች በደማቸው ውሰጥ ተጋልጠው እንደነበረም ምልክት የለም፡፡

የተለያዪ መላ ምቶች አሉ፡፡ ዋነኛው የነዚህ ሰዎች ሴሎች ቫይረሱን የማይቀበሉ አይነት ወይም ሴሎቹ በላያቸው ላይ ለቫይረሱ መግቢያ በር የሆኑ ሞሎኪሎች የላቸውም ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በሌሎች ለቫይረሱ መጋለጣቸው የታወቀ ግን በቫይረሱ ያልተለከፉ ሰዎችም ላይ ይታያል፡፡ ይህም በሥራ ምክንያት ለቫይረሱ የተጋለጡ የህክምና ባለሙያዎችንም ይጨምራል፡፡

አሁን በኤቸ አይ ቪ ህክምና የሚታይ የማያውቁ ሰዎችን የሚያስገርመው ሁኔታ ባልና ሚስት አንደኛቸው ቫይረሱ ሲኖርባቸው አንደኛቸው ሳይኖረባቸው መታየት ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ይህ እንግዲህ በተፈጥሮ በምንም አይነት መንገድ ለቫይረሱ ቢጋለጡም ቫይረሱን ሰውነታቸው ውስጥ እንዳይቀር የማድረግ የተፈጥሮ የመከላከያ ችሎታ ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ከዚህ ወገን ከሚመደቡ መሀከል ኤች አይ ቪ ካለባቸው ነብሰ ጡር ሴቶች የሚወለዱ ህፃናት ናቸው፡፡

የነዚህ በተፈጥሮአቸው በኤች አይ ቪ የማይለከፉ ሰዎች ቁጥር 15% ድረስ እንደሚሆን ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከኤች አይ ቪ ልክፍት ድኗል ተብሎ የሚታወቀው የበርሊኑ በሽተኛ በነበረበት የደም ካንሰር ምክንያት የራሱን የደም ሴሎች ጠርገው በማውጣት በምትኩ ከነዚህ በኤች አይ ቪ ቫይረስ አይለከፉም ከሚባሉ ሰዎች ደም በመውሰድ ትክ ስላደረጉለት ነው፡፡ ሰውየው አሜሪካዊ ነው፡፡ አስካሁን የኤች አይ ቪ መድሃኒት አይወስድም፡፡

በሌላ ርዕስ ደግሞ ቫይረሱን ማስወገድ ሳይችሉ ቀርተው የተለያየ መንገድ ሰለሚሄዱ ሰዎች እናካፍላለን፡፡

አንግዲህ ማን በተፈጥሮው በቫይረሱ እንደማይለከፍ ለማወቅ ምርምራ ስለማይደረግ ተገቢውን ጥንቃቄ ከማድረግ መቆጠብ ተገቢ አይደለም፡፡ በባልና ሚስት ወይም በጉዋደኞች መሀከል አንደኛቸው ሳይያዙ ቢቀርም ሚስጥሩ የተፈጥሮ ሁኔታ ሊሆን ቢችልም በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ ተገቢውን መከላከያ ማድረግ ተገቢ አንደሆነ አንመክራለን፡፡

በኢቮሉሽን ለሚያምኑ ሰዎች “Survival of the Fittest” የሚባለው ፍሬ ሀሳብ ይህንንም ይጨምራል፡፡ ኤች አይ ቪ ቫይረስ በአጣዳፊ አንደ ኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ አይነቶች ቶሎ የሚገድል ቢሆን ሳይሞቱ የሚተርፉ ሰዎች እንዳሉ ነው፡፡ በቅርቡ በኢቦላ ቫይረስ ያየነው ይህንኑ ነው፡፡

እንግዲህ ሳይንቲሰቶቹ የዚህን ምስጢር በመፍታት ኤች አይ ቪን ለማዳን በሚደረገው ጥረት ከተሰማሩ ስንብተዋል፡፡  ኤች አይ ቪን ማዳን የሚባል መርሆና እንቅስቃሴ እየጨመረ የመጣ ነገር ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ከክትባት ጀምሮ ሌሎች መድሃኒቶችን በመስጠት ሙከራው የቀጠለ ነው፡፡ ለዚህ ሙከራ በሙሉ ፈቃደኝነት በጥናቱ ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎችን ማመስገን ተገቢ ነው፡፡እሰከዚያ ድረስ በቫይረሱ የተለከፉ ሰዎች ሳይደበቁ መድሃኒት በመውሰድ የመከላከያ አቅማቸወን ገንብተው መቆየት ተገቢ ነው፡፡ ለጥቆማ ያህል በጥናቱ የሚሳተፉ ሰዎች መድሃኒታቸውን በመውሰድ ቫይረሱ በደም ውስጥ እንዳየዘዋወር በማድረግ (በሴሎች ውስጥ ግን ተደብቆ ይቆያል) የመከላከያ አቅማቸውን ገንብተው የሚገኙ ሰዎች ናቸው፡፡

በህክምና አለም ለሔፓታይትስ ሲ ቫይረስ መድሃኒት ይመጣል ብለን አስበን አናውቅም ነበር መጠቀም እስክንጀምር ድረስ፡፡ ኤች አይ ቪም ዕጣ ፋንታውን እንደሚያገኝ ተስፋ አለን፡፡ በመድሃኒቶች ምክንያት ያለውን ለውጥና የእድሜ መርዝመ በጎሽ ድረ ገፅ የተቀመጡትን ይመልከቱ፡፡  


​ኤች አይ ቪ  ያለባቸው ሰዎች ዕድሜ ጣራ ከሌለባቸው ሰዎች ጋራ እየተጠጋ ነው፡፡

በደንማረክ በተደረገ ጥናትና በቅርቡ አናልስ ኦፍ ኢንተርናል ሜዲሲን በተባለ መፅሔት በታተመው ዘገባ መሠረት፣ ኤቸ አይ ቪ ያለባቸው ሰዎች ነገር ግን የሚገባውን ህክምና የሚያገኙና መድሐኒታቸውን በትክክል የሚወስዱ ሰዎች የዕድሜ ጣሪያ ኤች አይ ቪ  ከሌለባቸው ሰዎች ጋራ እየተጠጋ ነው፡፡ ወደ ጥናቱ ዝርዝር ሳንገባ ውጤቱ ላይ ስናተኩር እንደ አጥኝዎቹ ግኝት በየአመታቱ የዕድሜ ጣሪያው እየጨመረ ሲሄድ ነው የታየው፡፡ ጥናቱን ተቀባይ የሚያደርገው ነገር የጥናቱ ቴክኒካል አቀራረብ፣ ከሌሎች ተመሳሳይ ጥናቶች ጋር ግኝቱ መስማማቱ ነው፡፡ ወደ ዕድሜ ቁጥር ከመሄዳችን በፊት ለዚህ የሚያበረታታ ውጤት ምክንያት ሆኖ የተገኘው በየጊዜው እየተሻሻሉ የሚሠሩት መድሀኒቶች አይነትና በቫይረሱ የተለከፉ ሰዎች ጥሩ ህክምና ማግኘት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የባህሪ ለውጥ በማሳየት ሰውነት ከሚጎዱ ነገሮች መቆጠብ ነው፡፡ ለምሳሌ በሌላ ጥናት የቀረበ ማስረጃ እንደሚያሳያው ኤች አይ ቪ ያለባቸው ሰዎች መድሃኒታቸውን በትክክለ እየወሰዱ ነገር ግን ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ የዕድሜ ጣሪያቸው ኤች አይ ቪ ይቀንስ ከነበረው በዕጥፍ ነው የሚሆነው፡፡ ማለትም ሲጋራ ማጨስ የበለጠ ጉዳት ያመጣል፡፡ ያነበበም የሰማም ስለ ሲጋራ ማጨስ ዕኩይነት መገንዘብ አለበት፡፡

ይህን ሁሉ ጉዳት እያመጣ እንዴት በሕጋዊነት እንደሚሸጥ ምክንያቱ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ሲጋራ መድሐኒት ነው ቢባል ከላቦራቶሩ ሳይወጣ እዛው ነበር የሚከለከለው፡፡ ወደ ኤች አይ ቪ ጥሩ ዜና ልመልሳችሁና የሚቀጥሉትን አሃዞች ላካፍላችሁ፡፡

ለምሳሌ በ25 አመት ዕድሜው በኤች አይ ቪ  ለተያዘ ሰው በየአመታቱ መኖር የሚችለው የዕድሜ ጣሪያ እየጨመረ ሲሄድ ነው የሚታየው፡፡

ከ1995 እሰከ 1996 የዕድሜ ጣሪያው 34.5 አመት

ከ1997- አስከ 1999 የዕድሜ ጣሪያው 52.2 አመት

ከ2000 እሰከ 2004 የዕድሜ ጣሪያው 62.8 አመት

ከ2005 አስከ 2009 ደግሞ 68.5 አመት

ከ2010 አስከ 2015 ደግሞ የዕድሜ ጣሪያው ወደ 73.9 አመት ከፍ ብሎ ተገኝቷል፡፡ ይህ ደግሞ ኤች አይ ቢ የሌለባቸው ሰዎች ከሚኖሩት ከ 79.4 - 80.8 ዕድሜ መጠጋቱ ነው፡፡

ዋናው መልክት በቫይረሱ አለመለከፍ ነገር ግን በቫይረሱ የመለከፍ አጋጣሚ ካለ በጊዜ መመርመርና መታወቅ ከዚያ ደግሞ ህክምና ክትትል በማድረግ መድሐኒቶችን በትክክል መውሰድ ነው፡፡

ስለ መድሐኒቶች መሻሻል ትንሽ ለማካፈል፤ በአሁኑ ጊዜ አብዛኘዎች በቫይረሱ የተለከፉ ሰዎች በቀን አንድ ኪኒን ብቻ ዕደግመዋለሁ አንድ ኪኒን ብቻ እንዲወስዱ ነው የሚጠየቁት፡፡ ለዚህም አንድ ኪኒን ብቻ ሆነው መታዘዝ የሚችሉ አምሰት አይነት መድሃኒቶች አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ችግር የሚፈጠረው መድሃኒትን በትክክል አለመውሰድ ብቻ ነው፡፡ ቫይረሱ በተለያዩ ምክንያቶች ጠንከር ብሎ ለተገኘባቸው ሰዎች ከሁሉት ኪኒኖችና ከዛም በላይ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ አንድ ኪኒን ቢሆንም በውስጡ ሶስት አይነት መድሃኒቶች አንድ ላይ ተቀምመው ይገኙበታል፡፡ የዛሪ ስንት አመታት በቀን ሶስት ጊዜ እፍኝ ሙሉ ኪኒኖች በሽተኞቻችን ይወስዱ ነበር፡፡ አዲሶቹ መድሃኒቶች መጠነኛ የሆነ የዳርቻ ጉዳት ሲኖራቸው፣ በትክክል ከተወሰዱ፣ ጥናቶችና የሥራ ተለምዶ እንደሚያሳየን ከ90ፐርስንት በላይ ቫይረሱን በቁጥጥር ሥር ያውላሉ፡፡ ዕውነት አንነጋገር ከተባለ በየስብሰባው ስንሄድ ሳይንቲሰቶቹን የምንጠይቀው ጥያቄ ቢኖር ቫይረሱን የሚያጠፋ ነገር መቼ እንደሚያገኙ ነው፡፡ ሙከራው እየቀጠለ ነው፡፡ ለሌላ ጊዜ ርዕስ እናደርገው እንጂ ሔፓታይትሰ ሲ የሚባል ቫይረስ በአብዛኛው በቀን አንድ ኪኒን ብቻ ለሶስት ወራት በመወስደ ቫይረሱ ከሰውነት እንዲጠፋ እየተደረገም እያደረግንም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከምርምር ጀምሮ እሰከህክምናው ድረስ በሙያው ላይ ሳለለሁበት ምስክርም አልሻም፡፡

እንግዲህ መድሀኒት እየወሰዱ የ74 አመት ዕድሜ ድረስ መኖር ትልቅ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ የቤተሰብ አባል ካለ ማበረታታት ተገቢ ነው፡፡ ቫይረሱ ለሌባቸው ሰዎች ይህ ግኝት ቀለል ብሎ ሊታይ ይችላል፣ ላለባቸው ሰዎች ግን የምሥራች ወሬ ነው፡፡

​መድሃኒታቸውን በትክክል የሚወሰዱ ኤች አይ ቪ ያለባቸው ሰዎች ረዥም እድሜ እንደሚኖሩ ተገለጠ
 
በቦሰተን ከተማ በየካቲት ወር በተደረገው ሰለ ኤች አይ ቪ ኮንፈረንስ ኤች አይ ቪ ያለባቸው ሰዎች መድሃኒታቸውን በሚገባ ከወሰዱ ረዥም እድሜ እንደሚኖሩ በካይዘር ፐርማነንቴ ሀኪሞች በቀረበው ጥናት ተገልጧል፡፡ ከዚህ ቀደም በ1996 የ20 አመት ወጣት ኤች አይ ቪ ቢኖረው ተጨማሪ እድሜ የሚያገኘው ግምት ለ19 አመታት ማለትም እስከ 39 አመት ድረስ ይኖራል ተብሎ ነበር፡፡ 
በ2011 ይህ ተጨማሪ እድሜ ተቀይሮ የሀያ አመቱ ወጣት ተጨማሪ 53 አመታት ማለትም እሰከ 73 አመት ሊኖር እንደሚችል ወይም አንደምትችል ከተነገረ ቆይቷል፡፡ 
በሳይነሳዊው አለም አንደሚደረገው ሁሉ የዚህ አይነት ስሌት በሚደረግበት ጊዜ ተጨማሪ ጥናት ይደረጋል፡፡ በዚህ መሠረት የካሊፎርንያ ካይዘር ፐርማነንቴ ሀኪሞች በኤች አይ ቪ የተለከፉ 25 000 ሰዎችንና ቫይረሱ የሌለባቸውን 250 000 ሰዎች ክትትል በማድረግ ሰዎች ምን ያህል እድሜ ሊኖሩ እንደሚቸሉ በሁለቱም ወገኖች ልዩነት መኖርና አለመኖሩን ለማረጋገጥ ጥናት አድርገዋል፡፡ 
በጥናቱ መሠረት የኤች አይ ቪ መድሀኒታቸውን በትክክል የሚወስዱ ሰዎች ዕድሜያቸው በመርዘም ከ50 አመታት በላይ መኖር እንደሚቸሉ ታይቷል፡፡ ረዥም እድሜ ለመኖር ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ሲኖሩ እነዚህ ልዪነት ሊያመጡ የሚችሉ ሁኔታዎች በጥናቱ ላይ የተለየ ውጤት እንዳይፈጥሩ በሁለቱም ወገን እኩል በሆነ ደረጃ እንዲታዩ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ኤች አይ ቪ ባለባቸውና በሌለባቸው ሰዎች የእድሜ ጣራ (Life expectancy ) ልዩነት ያለ ቢሆንም ኤች አይ ቪ ያለባቸው ሰዎች ግን ቀደም ብሎ ከታሰበው በላይ ረዥም እድሜ ሊኖሩ እንደሚቸሉ አንድሚኖሩም ተገልጧል፡፡

በፆታ ተለይቶ ሲታይ የ20 አመት እድሜ ያላት በኤች አይ ቪ የተለከፈች ሴት ተጨማሪ 51 አመት መኖር እንደምትችል ነው፡፡ ይህ ግን መድሀኒት በትክክል ለሚወስዱ ሰዎች መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ 
ወንድ ከሆነ ደግሞ ተጨማሪ 49 አመት ሊኖር እንደሚችል ነው፡፡ ኤች አይ ቪ ከሌለባቸው ሰዎች ጋር ሲወዳደር በሴቶችም ሆነ በወንዶቸ በኩል በእድሜ ጣራው ላይ የ13 አመት ልዩነት አለ፡፡ ማለትም ኤች አይ ቪ የሌለባቸው ሰዎች በ13 አመት ተጨማሪ የእድሜ ጣራ ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡

በዝርዝር ሲገለጥ ደግሞ የኤች አይ ቪ መድሓኒት በመወሰድ የሰውነት የመከላከያ አቅም መለኪያ የሆኑ ነጭ የደም ሴሎች በእንግሊዝኛ ሲዲ 4 ተብለው የሚጠሩ (CD4 ) በሕክምና አማካኝነት መጠናቸው ከ500 በላይ ከሆነ የእድሜ ጣራ ልዩነት በ13 አመት ሳይሆን ወደ 7.9 አመት ዝቅ ይላል፡፡ በነገራችን ላይ በሽታ ምልክት ታየም አልታየም ሲዲ4 ቁጥር 200 ና ከዛ በታች ከሆነ ኤይድስ ደረጃ ተብሎ ነው የሚታወቀው፡፡

በተጨማሪ አልኮሆል የማያዘወትሩ ወይም ያልተፈቀዱ መድሀኒቶችን የማይወሰዱ ኤች አይ ቪ ያለባቸው ሰዎች እድሜያቸው በመርዘም ከሌለባቸው ሰዎች ጋር ሲወዳደር የእድሜ ጣራ ልዩነቱ ወደ 6.8 አመታት ዝቅ ይላል፡፡ ሲጋራ የማያጨሱ ከሆነ ደግሞ ልዩነቱ ወደ 5.4 አመታት ዝቅ ይላል፡፡

ይህ በዚህ ህክምና ሙያ ለተሰማሩ ሰዎችና ለበሽተኞቻቸው ትልቅ የምስራች ነው፡፡ መልክቱ 
በጊዜ በኤች አይ ቪ መለከፍና አለመለከፍን ማወቅ
ቶሎ የኤች አይ ቪ ህክምና መጀመርና የሲዲ4 ቁጥርን ከ500 በላይ እንዲቆይ ማድረግ
ተጨማሪ ሁኔታዎች እንድ ሲጋራ ማጨስ አልኮሆል ማዘውተርን ማቆም
ያልተፈቀዱ ዕፆችን አለመውሰድ
ኤች አይ ቪ ህክምና ወይም መድሃኒት መውሰድ ዋናው ሚስጥር የታዘዘውን መድሃኒተ ያለ ማቁዋረጥ በየቀኑ መውሰድ ነው፡፡ ባቋረጡ ቁጥር ቫይረሱ ከተደበቀበት እየወጣ ሲዲ 4 ሴሎችን ቁጠር ይቀንሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መደሀኒቱ በየቀኑ ካልተወሰደ ቫይረሱ በመለማመድ መድሀኒቱን መቋቋም (Resistance ) ችሎታ ይፈጥርና መድሀኒቱ የማይሰራበት ደረጃ ይደርሳል፡፡
ኤች አይ ቪ ያለባቸው ሰዎች መድሀኒት አስከወሰዱ ድረስ እንደሌሎቸ ሰዎች የትምህርት የስራ ሌሎችንም በህይወታቸው ሊያደርጉ የሚፈልጉዋቸውን ነገሮች ማድረግ ይችላሉ፡፡ ትዳርና ልጅ መውለድ ይቻላል ፡፡ ከሀኪም ጋር በመካክር የሚደረግም ነገር ነው፡፡ይህ ደግሞ የዚህ ፅሁፍ ፀሀፊ በሙያው ምስክርነት የሚሠጥበት ነገር ነው፡፡
ወደፊት ኤች አይ ቪን የሚያድን ተስፋ እየጨመረ እየመጣ ነው፡፡ አስከዛው ድረስ ግን ህክምና መከታተል መድሃኒት መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ የሲዲ4 ቁጥር ከ500 በላይ ሆኖአል ብሎ መድሀኒት ማቆም ተገቢ አይደለም እንዳውም ስህተት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ መድሓኒቶች ለረዝም ጊዜ መወሰድ የሚችሉ በመሆናቸው እንኩዋን ለማቆም ሲዲ4 500ና ከዛ በላይ ለሆኑ ሰዎች መድሀኒት አንዲጀመር ከተወሰነ ሰንበት ብሏል፡፡
የኤች አይ ቪ ቫይረስ ከሲዲ4 ሴሎች ጉዳት ውጭ ሰውነት ላይ የሚያደረሰው የተለያዩ ሁኔታዎች እንዳሉ መታወቅ አለበት
ኤች አይ ቪ የለሌባቸው ሰዎች የሚያውቋቸውን ሰዎች ማበረታትና ድጋፍ መስጠት ተገቢ ነው፡፡
ቫይረሱን ወደሌሎች ሰዎች ከማስተላለፍ መቆጠብ ተገቢ ነው፡፡ እንግዲህ ኤች አይ ቪ ብቻ ሳይሆን ዚካና ኢቦላ የመሰሉ ቫይረሶች በግብረ ሥጋ ግንኙነት እንደሚተላለፉ መገንዘብ ተገቢ ነው