Health and History

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

በኤች አይ ቪ ለተያዙ ሰዎች በመርፌ በኩል በወር አንድ ጊዜ የሚሠጥ መድሐኒት

 
የኮቪድ ወረርሽኝ ትኩረታችን የያዘው ቢሆንም፣ ቀደም ባሉ በሽታዎች እንደ ኤች አይ ቪ ባሉት አንዳንድ የህክምና ዕደገቶች ወይም ለውጦች ታይተዋል፡፡ ለጊዜው ለማለፍ ብሞክርም፣ አንዳንድ አንባቢዎች የኤች አይ ቪን መድሐኒት በተመለከተ የተሣሣተ መረጃ ለህብረተሰቡ እየሠጡ መሆኑን በመገንዘብ ይህንን ርዕስ ለማካፈል ወሰንኩ፡፡

መደበኛው የኤች አይ ቪ (HIV) ወይም ኤይድስ (AIDS)  ህክምና የተለያዩ መድሐኒቶችን በየቀኑ በመውሰድ ቫይረሱን በሰውነት ውስጥ በቁጥጥር ሥር ማዋል ነው፡፡ ቫይረሱን መቆጣጠር ከተቻለ የተለያዩ ጥሩ ውጤቶች ይከተላሉ፡፡ በመጀመሪያ የሰውነት መከላከያ አቅም እየጠነከረ ሰለሚሄድ ሰዎች ከኤይድስ ደረጃ በሽታ መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ጤናማ ደረጃ ሰለሚደርሱ የዕድሜ ጣሪያቸው በኤች አይ ቪ ካልተያዙ ሰዎች ጋር የተቀራረበ መሆኑ ነው፡፡ ይህ የዕድሜ ጣራ ከፍ ማለት ከታየ ቆይቷል፡፡


ሁለተኛ፤ በመድሐኒቶቹ አማካኝነት ቫይረሱ በቁጥጥር ሲውል፣ በደም ምርመራ ላይ ላቦራቶሪው ቫይረሱን መቁጠር ሳይችል ሲቀር በእንግሊዝኛ (undetectable) ወይም ከተወሰነ መለኪያ ቁጥር በታች ነው የሚል ሪፖርት ይልካል፡፡ ሀኪሞችም ሆነ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ይህንን ሪፖርት ነው የሚፈልጉት፡፡ አስተውላችሁ ከሆነ ሰዎችን በቫይረሱ የተያዙ ነው ያልኩት፡፡ በሽተኞች አላልኩም፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንደጠቀስኩት መድሐኒታቸውን በትክክል ከወሰዱ የበሽታ ስሜት ቀርቶ የዕድሜ ጣሪያቸው ከሌሎች ጋር ይቀራረባል፡፡


በመድሐኒቱ ምክንያት ቫይረሱ undetectable ደረጃ ሲደርስ፣ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቫይረሱን ወደ ሌላ ሰው አያስተላልፉም፡፡ ለዚህም ነው በእንግሊዝኛ undetectable = Untransmissible, (U=U) የሚባለው፡፡

የዚህ Undetectable ደረጃ ዋና ጠቀሜታ ወይም አገልግሎት የሚታየው በኤች አይ ቪ ቫይረሰ ተይዘው ነብሰ ጡር ለሆኑ ሴቶች፣ መድሐኒት በመጀመር ቫይረሱን በመቆጣጠር ወደ ፅንሱ እንዳይሻገር በማድረግ የሚወለዱት ልጆች ከቫይረስ ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉ ነው፡፡ የዕለት ከዕለት ሥራችንም ሰለሆነ ብዛት ያላቸው ከቫይረሱ ነፃ የሆኑ ህፃናት ለመወለዳቸው ምሥክር ነን፡፡

ታዲያ ቀደም ብሎ የመጡት መድሐኒቶች የዳርቻ ጉዳታቸው ከፍተኛ ሰለነበር መድሐኒቶች በየጊዜው እየተሻሻሉ በመሠራታቸው መድሐኒቱን የሚወስዱ ሰዎች ለረዥም ጊዜ የሚወሰዷቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ሌላው መሻሻል የታየው ደግሞ የሚወሰዱ እንክብሎች ቁጥር መቀነስና በቀን እስከ ሶስት ጊዜ ይወሰዱ የነበሩ መድሐኒቶች በአብዛኛው በቀን አንድ ጊዜ አለዚያም በቀን ሁለት ጊዜ እንዲሆን መደረጉ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቸ የሚወስዷቸው መድሐኒቶች፣ የተለያዩ መድሐኒቶችን ባንድ ላይ በአንድ እንክብል በመቀመም፣ አንድ ኪኒን ብቻ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በውነት የቀረው ነገር ቢኖር ከቫይረሱ የሚፈውስ መድሐኒት አለመድረሱ ነው አንጂ በጣም ብዙ ለውጦች ተደርገዋል፡፡

ይህም ሆኖ አንዳንድ ሰዎች በየቀኑ መድሐኒት መውሰድ የተሰላቹ ወይም በየቀኑ መውሰድ የሚገባቸውን መድሐኒት እየረሱ ቸግር ሲፈጠር ታይቷል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የታሰበውን ቫይረሱን የመቆጣጠር ደረጃ ላይደረስ ይችልና እንዲያውም ቫይረሱ መድሐኒቱን በመላመድ የመድሐኒቱን አቅም መቋቋም የሚችልበት ደረጃ ይደርስና መድሐኒቱን እንደማይሠራ ያደርገዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በእንግሊዝኛ viral resistance ይባላል፡፡ ቫይረሱ እዚህ ደረጃ የሚደርሰው መደሐኒቱ ኢላማ ያደረጋቸውን የቫይረሱ ፕሮቲኖችን በመቀየር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በእንግሊዝኛ mutation ይበላል፡፡ ቫይረስና mutation እንግዳ እንዳልሆነባችሁ እገምታለሁ፡፡ ዕድሜ ለኮሮና ቫይረስ፡፡ አዲስ ዝርያም የሚፈጠረው በዚህ መንገድ ነው፡፡

ታዲያ ለተሠላቹና ለሚረሱ ሰዎች፣ ኪኒን የሚባል ነገር መውሰድ ለማይፈልጉ ወይመ ለማይችሉ ሰዎች፣ አንደኛ በሰውነት ውስጥ ለረዥም ጊዜ መቆየት የሚችል ሁለተኛ በመርፌ መልክ የሚሠጥ መድሐኒት ለአገልግሎት ለማቅረብ ኩባንያዎች ሲሰሩ መክረማቸውን እናውቃለን፡፡

ከነዚህ መሀል አንደኛው የተሳከ ደረጃ በመድረሱ በጃንዋሪ 2021 ፈቃድ አገኘ፡፡ ሰለመድሐኒቱ አንድ ሁለት ልበል

በእንግሊዝኛ Cabenuva ይባላል፡፡ የሁለት መድሐኒቶች ጥምር ነው፡፡ አንደኛው መድሐኒት አሁን በአፍ የሚወሰድ አገልግሎት ላያ ያለ rilpivirine (Edurant) የሚባል ሲሆን ሌላኛ ደግሞ cabotegravir ይባላል፡፡ ሁለተኛው አዲስ መድሐኒት ቢሆንም የዚህ መድሐኒት ወገን የሆኑ ሌሎች በአፍ የሚወሰዱ ከአራት በላይ የሚሆኑ በአገልግሎት ላይ ያሉ መድሐኒቶች አሉ፡፡

በመርፌ በኩል የሚሠጠው ይህ መድሀኒት cabotegravir/rilpivirine በንግድ መጠሪያ ስሙ ከላይ እንደተጠቀሰው cabenuva ይባላል፡፡

ይህ መድሀኒት የሚሠጠው ወይም የተፈቀደው በኤች አይ ቪ ቫይረስ ለተያዙ ሰዎች አሁን አየወሰዱ ያሉትን መድሐኒቶች ለመተካት ሲሆን፣ አንደኛ ሰዎቸ መድሐኒት እየወሰዱ ቫይረሱን በቁጥጥር ሥር ያደረጉ፣ ሁለተኛ ደግሞ ከዚህ በመርፌ መልክ የሚሠጠውን መድሐኒት ከዚህ ቀደም በአፍ ወስደው ከነበረና ቫይረሱ ለመድሐኒቱ resistance የሌለው መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ቫይረሱ resistance ባይኖረው እንኳን ለምሳሌ በመርፌ መልክ ከተዘጋጀው መድሐኒት አንዱን rilpivirine በአፍ እይወሰዱ እያለ ባለመሥራቱ ምክንያት ወደ ሌላ መድሐኒት ተቀይሮላቸው ከሆነ፣ መርፌ ለነዚህ ሰዎች አይሠራም፡፡

ሰዎቹ መርፌውን ከመጀመራቸው በፊት ግን፣ የመርፌውን መድሀኒቶች በእንክብል መልክ በአፍ ለአንድ ወር እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ ይህም መድሐኒቱ በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የማያመጣ ወይም ሰዎቹ የሚሰማቸው ነገር አለመኖሩን ለማወቅ ነው፡፡ አለዚያ ለአንድ ወር በሰውነት ውስጥ የሚቆይ መድሐኒት ተሠጥቶ ሰዎቹ ላይ ጉዳት ቢያስከትል መድሐኒቱ ከሰውነት አስከሚወገድ ድረስ ችግር ይፈጠራል፡፡

ለአንደ ወር በአፍ ወስደው ምንም ችግር ካልታየ፣ በመርፊ በኩል የሚሠጠው መድሐኒት ይጀመርና፣ ሰዎቹ በየወሩ መርፌውን እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ እንግዲህ በዚህ በመርፌ በኩል የሚሠጠውን መድሐኒት የሚወስዱ ሰዎች በአፍ የሚወሰዱ መድሀኒቶችን ያቆማሉ ማለት ነው፡፡ ልብ በሉ፣ ጠቀሜታው ይህ ነው እንጂ ቫይረሱን ጠርጎ በማውጣት ማዳን ወይም ፈውስ ማምጣት አይደለም፡፡

ይህንን መድሐኒት ለመጀመር መመዘኛዎችን አልፎ እንጂ ለሁሉም በኤች አይ ቪ ለተያዙ ሰዎች የሚሠጥ አይደለም፡፡ መድሐኒቱ ለአዋቂዎች ብቻ ነው የተፈቀደው፡፡ መመዘኛው ላይ ይህ መድሐኒት ሰዎቹ ለሌላ ተጓዳኝ በሽታ ከሚወስዷቸው መድሐኒቶች ጋር የመይጋጭ መሆኑን መረጋገጥ አለበት፡፡ ሰለዚህ በኤች አይ ቪ የተያዙ መድሐኒት እይወሰዱ ያሉ ሰዎች ይህንን በመርፌ መልከ የሚሠጠውን መድሐኒት መውሰድና አለመውሰድ መቻላቸውን ከሀኪሞቻቻው ጋር መመካከር አለባቸው፡፡ ማስታወስ የሚገባቸው ነገር ግን፣ ይህ መርፌ አሁን እየወሰዱ ላሉት መድሐኒት ትክ በመሆን ለረዥም ጊዜ ያለማቋረጥ የሚወሰድ መሆኑን ነው፡፡

ሌላው በመርፌ መልክ እንዲሠጥ የተፈቀደው አዲስ መድሐኒት፣ በቫይረሱ ለተያዙ ሰዎች ሳይሆን ቫይረሱ እንዳይዛቸው ለመከላከያ የሚሆን ነው፡፡ ይህ ርዕስ ሰፋ ሰለሚል በሌላ ፅሁፍ እንገናኝ፡፡

ማጠቃለያው ኤች አይ ቪን (HIV) የሚያድን አዲሰ መድሐኒት ገና አልመጣም፡፡ አንባቢዎቸ በማሠራጫ ሜዲያቸው ይህንን ካሉ ሥህተት መሆኑን አምነው ለአዳማጮቻቸው እንዲነግሩ ምኞቴ ነው፡፡

መልካም ንባብ፣ አካፍሉ!

Community health 

education in Amharic