Cholera ኮሌራ
አንድ የህክምና ስብሰባ ላይ ከደቡብ አሜሪካ አገሮች ከአንደኛው የመጣ የሥራ ባልደረባ ሀኪም ጋር ስንጨዋወት፣ የኮሌራ ነገር ተነሣ፡፡ የሚገርመው እራትም ልንበላ እየተዘጋጀን ነበር፡፡ በጭውውታችን ዋናው ቁም ነገር እናም እንደ ዶክተሩ ባልደረባዬ አገላለፅ፣ በሁለት የላቲን አሜሪካ አገሮች ኮሌራ ተከስቶ ነበር፡፡ አንደኛው አገር በቂ ዝግጅት በማድረግ በየቦታው የሰውነት ድርቀት መከላከል የሚችል የሚጠጣ ፈሳሽ አስቀምጠው ነበር፣ ሌላው አገር ግን ይህንን ማድረጉም ትዝ አላላቸውም ነበር፡፡ ኮሌራው ሲያባራ፣ የሚጠጣውን ፈሳሽ ባዘጋጀው አገር በኮሌራ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ሲሆን ባልተዘጋጀው አገር ግን ቁጥር ስፍር የሌለው ሰው አልቋል ብሎ አጫወተኝ፡፡
ከዚህ በመነሳት ለምን ትንሽ ትምህርታዊ ፅሁፍ አይቀርብም በሚል መንፈስ ሰለ ኮሌራ መጠነኛ ምክርና ትምህርት ለማካፈል እንደተለመደው በጎሽ ድረ ገፅ ቀርቧል፡፡
ለመሆኑ ኮሌራ ምንድን ነው? በተለያዩ ጊዜያት በተለያዪ የአለም ክፍሎች የዚህ በሽታ ወረርሽኝ መከሰትና የብዙ ሰዎች ህይወት መጥፋት ይነገራል፡፡ ኮሌራ፣ ቪብሪዮ ኮለሪ በሚባል ባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰት አጣዳፊ የተቅማጥ በሽታ ነው፡፡ በየአመቱ ከመቶ ሺ በላይ ሰዎች ህይወታቸው በዚህ በሽታ ምክንያት እንደሚያልፍ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከሶስት አስከ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በየአመቱ እንደሚለከፉ ነው፡፡
ይህ በሽታ በአብዛኛው ቀለል ያለ ብዙም ምልክት የማይሰጥ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በጣም ብርቱ ይሆናል፡፡ ብርቱ በሚሆንበት ጊዜ፣ ሰዎች ማቆሚያ የሌለው የሚመስል ከባድ ተመላላሽ ተቅማጥና ትውኪያ ይኖራቸዋል፤ የሰው ሕይወት ማለፍ ምክንያት የሚሆነው ይህ እንደ ጎርፍ የሚወርደው ተቅማጥና ትውከት የሰውነት ድርቀት በማስከተል የሰውነት መሳት ወይም ሾክ ወስጥ በማስገባት ነው፡፡
ኮሌራ የት ነው የሚገኘው?
ይህ ባክቴሪያ በኮሌራ ከተለከፈ ሰው ከሚወርድ አይነ ምድር ወይም ተቅማጥ ጋር ንክኪ ባለበት ውሀ ወይም ምግብ ላይ ይገኛል፡፡ እንግዲህ የሠገራ ወይም የአይነምድር ወራጅ ፈሳሽ ሰዎች የሚኖሩበትን አካባቢ በሚያጥለቀልቅበት ስፍራ የሚጠጣ ውሃና ምግብን መበከል ይችላል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ጋራ በተያያዘ፣ በቂ ለንፅህና የሚሆን ውሀ እጥረት ወይም አለመኖር፣ ቆሻሻ በሥነሠርአት የማይወገድበት በታ ወይ የአካባቢ ንፅህና በጎደለባቸው ቦታዎች፣ ወይም ደግሞ ለመጠጥ የሚቀርበው ውሃ በበቂ መጠን ወይም ተገቢውን ሕዋሳትን ለማስውገድ የሚጨመሩ ኬሚካሎች በማይደረግባቸው ቦታዎች ነው ኮሌራ ሊከሰት የሚችለው፡፡
የኮሌራ በሽታን የሚያስከትለው ባክቴረያው ንፅህና ከጎደለባቸው ቦታዎች በተጨማሪ፣ በተፈጥሮ ጨውነት ያለባቸው ውሃዎችና የባህር ዳርቻዎች ይኖራል፡፡ በዚህ ምክንያት ከባህር ምግቦች አንዱ የሆነው ሼል ፊሽን በጥሬው መብላት በዚህ ባክቴሪያ መለከፍን ያስከትላል፡፡በዚህ ምክንያት በበለፀጉ አገሮችም በሽታው ሊከሰት ይችላል፡፡
ታዲያ አንድ ሰው እንዴት ነው በኮሌራ ሊለከፍ የሚችለው የሚለው ጥያቄ መነሳቱም የግድ ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በኮሌራ ባክቴሪያ የተበከለ ምግብ በመብላት ወይም ውሀ በመጠጣት አንድ ሰው ወይም ሰዎች በባክቴረያው በመለከፍ በበሽታው ይያዛሉ፡፡ ለብዙ ወረርሽኝ መነሳት ምክንያቱም በባክቴሪያው የተለከፈው ሰው ሠገራ የመጠጥ ውሀን ሲበክል ነው፡፡ የመጠጥ ውሃን በቂ የሆነ ኬሚካል አለማድረግ፣ ወይም የአይነምደር ፍሳሽን አለመቆጣጠር በሽታውን በፍጥነት እንዲዛመት ያደርገዋል፡፡ መገንዘብ ያለብን ነገር ቢኖር በሽታው የሚተላለፍው ከላይ እንደተገለፀው የተበከለ ምግብና ውሀን በመጠቀም እንጂ ከሰው ወደ ሰው ከታመመ ሰው ጋር በሚደረጉ ንኪኪዎች አይደለም፡፡ ነገር ግን የታመመው ሰው ተቅማጥ የሚጠጣ ውሃና ምግብን እንዳይበክል መጠንቀቅ ያሰፈልጋል፡፡
አንድ ሰው በበሽታው ከተለከፈ ምን አይነት ስሜትና ምልክቶች ይኖሩታል?
በአብዛኛው ቀለል ያለ ስሜት ሲኖር አስር በመቶ በሚሆኑ ሰዎች ግን በሽታው የበረታና የከፋ በመሆን ከመጠን በላይ ተቅማጥና ትውከት ምክንያት የሰውነት ድርቀት በማስከተል እርዳታ ካልተደረገ በስተቀር የህይወት እልፈት ያስከትላል፡፡ ይህ ደግሞ በሰአታት ውስጥ ነው የሚከሰተው፡፡ ታዲያ አንድ ሰው በባክቴሪያው ከተለከፈ በኃላ በምን ያህል ጊዜ ነው የበሽታ ስሜትና ምልክት የሚሰማው ወይም ወደ በሽታ የሚቀየርበት? ይህ ደግሞ የተለያዬ የጊዜ መጠን ነው ያለው፤ ማለትም በትንሽ ሰአታት ውስጥ የበሽታ ምልክት ሊታይ ይችላል አለዚያም ከአምሰት ቀናት በኋላም ሊሆን ይችላል፡፡ ከአምስት ቀናት በኋላ ወደ በሽታ በሚቀየርበት ጊዜ ሰዎች የት ቦታ እንደተለከፉ በውል ማወቅ ሊቸግራቸው ይችላል፡፡ ሆኖም በአብዛኛው የበሽታው ምልክት የሚታየው ሰዎች በባክተሪያው ከተለከፉ ከሁለት ወይም ከሶስት ቀናት በኋላ ነው፡፡ እንግዲህ ንፁህ የሆነ የመጠጥ ውሃ በሌለበት፣ ቆሻሻ በስነስርአት በማይወገድበት፣ ሰዎች ደግሞ በቂ የሰውነት ንፅህና ማድረግ በማይችሉበት ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ለዚህ በሽታ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡
በበሽታው የተያዙ ከመሰለዎት ወይም የቤተሰብ አባል ከተያዘ በአስቸኳይ ህክምና መፈለግ ተገቢ ነው፡፡ ዋናው አደጋ የሚመጣው በተቅማጥ ምክንያት በሚከሰተው የሰውነት ድርቀት ስለሆነ፣ ይህም በሰኣታት ውስጥ ለህይወት እልፈት የሚዳርግ ስለሆነ፣ ከሰውነት የሚወጣውን ፈሳሽ በመተካት ለህይወት አስጊ የሆነውን የሰውነት ድርቀት መከላከል ቅድሚያ የሚሰጠው እርምጃ መሆን አለበት፡፡ ይህን የሰውነት ድርቀት ለመከላከል በአፍ የሚጠጣ በእንግሊዝኛ oral rehydration solution (ORS) ከተገኘ ወዲያውኑ መጀመር አለበት፡፡ ወደ ሆስፒታልም መንገድ ቢጀምሩ ይህ ፈሳሽ መወሰድ አለበት፡፡ በዚህ መንገድ የሰውነት ድርቀትን መቀነስ ወይም መከላከል ይቻላል፡፡ ጡት የሚጠባ ህፃን ከሆነ እያስቀመጠውም ቢሆን ጡት ማጥባት መቀጠል አለበት፡፡ የኮሌራ ህክምና ዋናው የወጣን ፈሳሽ መተካት ነው፡፡ ፀረ ህዋስ መድሀኒት ከበሽታው ቶሎ እንዲያገግሙ የሚረዳና የበሽታወን አስከፊነት የሚቀንስ ቢሆንም ህይወት የሚያድነው ዋነኛው ነገር ፈሳሽን መተካት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ወዲያውኑ ከተጀመረ በኮሌራ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከአንድ ፐርሰንት በታች ያደርገዋል፡፡ ከሀይለኛ ተቅማጥ ጋር ትውኪያ ያለው ሰው በአፍ የሚጠጣውን ፈሳሽ መውሰድ ስለማይችል በአስቸኳይ ወደ ህክምና ቦታ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ በህክምና ቦታው በክንድ መርፌ የሚሰጥ ፈሳሽ እንዲያገኙ በማድረግ የሰውነት ድርቀትን መከላከል ይቻላል፡፡
በሽታው የተበከለ ምግብና መጠጥ በመጠቀም የሚተላለፍ ስለሆነ የታመመ ሰው ስለነኩ በበሽታው አይያዙም፡፡
በበሽታው ላለመያዝ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች
ኮሌራ ተከሰተ በሚባልበት ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ወይም ወሰ ቦታው የሚጓዙ መንገደኞች ማድረግ የሚገባቸው ነገሮች
የሚጠጡት ውሀ የታሸገ፣ ወይም ፈልቶ የቀዘቀዘ፣ የታሸጉ የለስላሳ መጠጦችን መጠቀም፣ መሆን አለበት፡፡ በቂ የሆነ ባክቴሪያዎችን መግደል የሚችል ኬሚካል የተደረገበት ውሃ መጠቀም ይቻላል፡፡
የቧንቧ ውሀ መጠጣት፣ በረዶን መጠጥ ላይ መጠቀም መደረግ የለበትም፡፡
በየጊዜው እጅን በንፁህ ውሃና በሳሙና መታጠብ፤ ውሀ ከሌለ ደግሞ አልኮል ያለባቸው የእጅ መፀዳጃዎች መጠቀም ይቻላል (የአልኮል መጠኑ ቢያንስ 60 ፐርሰንት መሆን አለበት፡፡
እጅዎን መታጠብ ወይም ማፅዳት ያለብዎት፣ ከመመግብዎ በፊት፣ ከተፀዳዱ በኋላ፣ ምግብ ከማዘጋጀትዎ በፊት መሆን አለበት፡፡
የምግብ ቁሳቁሶችን ለማጠብ፣ ምግብ ለማዘጋጀት፣ በረዶ መስራት ካስፈለገ፣ ጥርስ ለመቦረሽም ቢሆን ቢቻል የታሸገ ውሀ ወይም የፈላ አለዘያም በቂ ኬሚካል የተደረገበት ውሀ መሆን አለበት፡፡
የሚመገቡት መግብ የተጠበሰ ወይም የተቀቀለ ሆኖ በትኩሱ መሆን አለበት፡፡ ያልበሰለ ወይም ጥሬ ምግብ ከመመገብ ይቆጠቡ፤ የታሸጉ ምግቦች አስተማማኝ ከሆኑ መጠቀም ይቻላል፡፡ ፍራፍሬ ከሆነ ራስዎ የላጡት መሆን አለበት፡፡ ጥሬ ምግብ ቅጠላቅጠሎችን ይጨምራል፡፡
የአይነምድርን ወይም ሠገራን የመጠጥ ውሀን፣ የመስኖ ውሀን በማይበክል ሁኔታ በአግባቡ መወገድ አለበት፡፡ ሜዳ ላይ መፀዳዳት ተገቢ አይደለም፡፡ ሁል ጊዜ እንደምንጠቅሰው ተላላፊ በሽታ የህብረተሰብ ችግር ነው፡፡ ዝም ብሎ ከማለፍ ሌሎችን ማስተማርና ማስረዳት ተገቢ ነው፡፡ በሠፈርና በአካባቢ አይነምድርና ቆሻሻዎች በአግባቡ የሚወገዱበትን ሁኔታ መምከርና መተባበር ከኮሌራ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል ወይም ማስቀረት ያስችላል፡፡ ንፅህና ከአካባቢ መጀመር አለበት፡፡
በመጨረሻም በአፍ የሚወሰዱ ሁለት የክትባት አይነቶች መኖራቸውን መግለፅ ቢያስፈልግም፣ ክትባቶቹ የት እንደሚገኙ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ክትባት ወሰዱም አልወሰዱም ዋናው ነገር ከላይ የተጠቀሱትን ጥንቃቄዎች ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
መልካም ንባብ
Community health
education in Amharic
ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ