አወዛጋቢ የሆነው በስኳር ኢንዱስትሪ
የተጠናው ጥናት ተጋለጠ
እንደ ትምባሆ ኢንዱሰትሪ ሁሉ፣ የስኳር ኢንዱሰትሪ፣ ስኳር በጤንነት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በመሸፋፈን አልፎም ጥርጣሬ እንዲኖር በማድረግ ሲነግዱ መክረማቸው ግልፅ ነው፡፡ ይህን በሚመለከት ጎሽ በድረ ገፁ አስፍሯል፡፡ ከዚህ ቀደም ሚስጥራዊ በሆን መንገድ ለጤንነት ችግር የሚያሰከትለው ስኳር ሳይሆን ጮማ ነው ተብሎ እንዲወቀስ ማድረጋቸው የሚረሳም አይደለም፡፡
አሁን በቅርቡ በተጋለጠ ጥናት የስኳር ኢንዱስትሪ ራሳቸው ጥናት እንዲጠና አስደርገው ነገር ግን የጥናቱ ውጤት ስኳር ችግር የሚያመጣ መሆኑን ስለሚገልፅ ጥናቱ እንዳይታተምና ለህዝብ እንዳይዳረስ አስደርገዋል፡፡ በመሠረቱ ጥናት ሲካሄድ ውጤቱ ምንም ይሁን ለህዝብ መቅረብ አለበት ወይም ነበረበት፡፡
በ1960 እኤአ በከፍተኛ የስኳር መጠንና በኮለስትሮልና ስለሚያስከትለው ካንሰር በአይጦች ላይ የተደረገ ጥናት ነበር፡፡ ይህ ጥናት እንዲካሄድ ያስደረገው የስኳር ኢንዱስትሪው ነበር፡፡ ጥናቱ ደግሞ ፕሮጀክት 259 ተብሎ ይጠራል፡፡ ልብ በሉ ይህ ጥናት የዛሬ 50 አመት ነው የተጠናው፡፡
ይህ የስኳር ኢንዱስትሪውን ያላስደሰተው ጥናት ውጤት ያሳየው፣ ከፍተኛ የስኳር መጠን የተመገቡት አይጦች ከሌሎቹ ብዙ ስኳር ካልተመገቡት ወይም መደበኛ ምግብ ከተመገቡት አይጦች ጋር ሲወዳደር፣ በሽንታቸው ቤታ ግሉኮዩሪኒዴዝ የተባለ ኮምፓውንድ እንደተገኛባቸው ነው፡፡ ይህ ኮምፓውንድ ወይም ኤንዛይም ደግሞ የሽንት ፊኛ ካንሰር ጋር የተያያዘ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ የስኳር መጠን መመገብ በአንጀት ውስጥ የሚገኘውን ጤናማ የሆነ የባክቴሪያ ኑሮ ያዛባል፡፡ ይህ በአንጀት የሚገኘው ጤናማ የባክቴሪያ መጠን ወይም አይነት ሲዛባ ሰውነት ላይ ችግር እንደሚያስከትል ይታወቃል፡፡
ይህንን ጥናት ሰፖንሰር ያደረገው የስኳር ኢንዱስትሪ ውጤቱን እንዳየ የገንዘብ ምንጩን በማቆም ጥናቱ እንዳይወጣ አስደርጓል ነው ክሱ፡፡ እንግዲህ በአሜሪካ ህግ መሠረት በሰውነት ላይ ካንሰር የሚያመጡ ምግብ ላይ የሚጨመሩ ነገሮች በሙሉ ይክለከላሉ፡፡ ይህ የዴላኒ አንቀፅ(Delany Clause) ተብሎ የሚጠራው ህግ በ1958 የፀደቀ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ደግሞ የአሚሪካው የምግብና የመድሐኒት አስተዳደር ወይም (FDA) ካንሰር ያሰከትላል የሚባል ኮምፓውንድ ያለበት ምግብ ለሽያጭ ወይም ለህዝብ እንዳይቀርብ ያሳግዳል፡፡
ታዲያ በጊዜው የነበረው የስኳር ኢንዱስትሪ ያን ከማድረጉ በተጨማሪ፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የስኳር ማሕበር የዚህን ጥናት ውጤት ማስተባበል ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል፡፡
ዋናው መልክት ማስጠንቀቂያውን ማዳመጥና ከፍተኛ የስኳር መጠን ካላቸው ምግቦችና መጠጦች መራቅ ነው፡፡ በአንደዚህ አይነት ሁኔታ አትራፊዎችን ማመን ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ እነ ሶዳና ሌሎች የፋብሪካ ጭማቂዎችን መሰናበት ጥሩ ነገር መሆኑንም እንጠቁማለን፡፡ ሙሉ ፍራፍሬዎችን እየገዙ ቤት ውስጥ መጭመቅ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ ውሀ፣ ሻይና ቡና መች ከፉና፡፡
በእርግጥም ለወሊድ መቆጣጠሪያ የሚሆን ክትባት አለ
በወሬ በወሬ እየሰማን ጉዳዩን ብዙም ትኩረት አልሠጠነውም ነበር፡፡ የሚያመክን ክትባት አለ ሲባል፣ የመጀመሪያው ጥያቄ ውነት ነው ወይ የሚለው ነው፡፡ ከጓደኛዬ ጋራ ሀሳብ ስንለዋወጥ፣ ክትባቱ በስህተት ማምከን የሚችል መድሐኒት ጋር ተነካክቶ ይሆናል ወይም እንደዚያ የሚባል ነገር ሰምቻለሁ ነው፡፡ ነገሩ ትንሽ የሚከነክን ስለሆን በወሬ በወሬ ሳይሆን በሳይንሳዊ መንገድ የተሠሩ ጥናቶችን ለእንባቢ የሚያቀርቡ የህክምና ወይም የጤና መፅሔቶችን ማገላበጥ ጀመርኩ፡፡ እና እራሴንም አስከሚገርመኝ ድረስ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ፅሑፍ አገኘሁ፡፡ ለካስ አዳማጭና አንባቢ ጠፍቶ ነው እንጂ ለወሊድ መከላከያ የሚሆነው ክትባት ከተሠራ ስንብቷል፡፡
በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1993 የታተመው አናልስ ኦፍ ኢንተርናል ሜዲሲን የሚባል መፅሔት ላይ በቁጥር Ann Med. 1993 Apr;25(2):207-12 ላይ የወጣ መረጃ በዚያን ጊዜ በህንድ አገር ለዚሁ ወሊድ ለመከላከል ታስቦ የተሠራ ክትባት እንዳለ ይገልፃል፡፡
ክትባቱ እንደተባለው ለቴታነስ ወይም ዲፍቴሪያ በሽታ መከላከያ በሚሠጠው ክትባት ላይ ተደርቦ የተሠራ ነው፡፡ በውስጡም HCG የተባለው ሆርሞን ክፍሎች ያሉበት ሆኖ፣ አላማው ክትባቱ በሚሠጥበት ጊዜ፣ የሰውነት ክፍላችን ለዚሁ HCG አጥቂ የሆነ አንቲ ቦዲ እንዲፈጥር ነው፡፡ እንግዲህ HCG (Human Chorionic Gonadotriphin) ለእርግዝና ከሚያሰፈልጉ ሆርሞኖች በጣም ወሳኝ የሆነ ነው፡፡ በክትባቱ ምክንያት የራስ ሰውነት ይህንን ሆርሞን ማጥቃት ሲጀመር እርግዝና እንዳይፈጠር ያደርጋል ማለት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ይህ ሁኔታ በጥናት ላይ እንደነበረና ደረጃ ወይም ክፍል ሁለት የሚባለውን የጥናት ክፍል እንዳለፈ ነው የጥናቱ ፀሐፊዎች ያሰፈሩት፡፡ በዚህ መሠረት ሴቶች ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ ማርገዝ አለመቻላቸው እንደጥሩ ውጤት ሆኖ ተዘግቧል፡፡ የኔም የግሌ ጥያቄ የነበረው፣ ይህ ነገር ቋሚ መካንነት ያስከትላል ወይ ነው፡፡ እንደ ጥናቱ ዘጋቢዎች፣ ይህ ሁኔታ ሊሚለስ ይችላል ነበር፡፡ ያ እንግዲህ በዚያን ጊዜ ነው፡፡
ዋናው ጥያቄ ክትባቱ ሲሰራና ተያይዞም አላማው ግልፅ በሆነ መንገድ እርግዝና መከላከያ ሆኖ ሲሆን፣ ክትባቱ የሚሠጣቸው ሰዎች የክትባቱ አላማ ተነግሯቸዋል ወይ ወይም አስቀድሞ ተገልፆላቸዋል ወይ ነው፡፡ እየተነገራቸው የተከተቡ ሰዎች ካሉ ምንም የሚያከራክር ነገር አይሆንም፡፡ ነገር ግን በሽፍን ሳይገለፅላቸው ክትባቱ እየተሠጠ ከሆነ ሌላ ጥያቄ ነው፡፡
በዚህ መፅሔት ዘገባ መሠረት ለወሊድ መቆጣጠሪያ ታስቦ የሚሠራ ክትባት መኖሩና ይህም ክትባት ለቴታነስና ለዲፍቴሪያ በሽታ መከላከያ በሚሰጠው ክትባት ላይ ተደርቦ እንደሚሠጥ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይሀ የፀረ ክትባት አቋም ያላቸው ሰዎች የሚያናፍሱትም ወሬ አይደለም፡፡ በመሠረቱ እኔ ራሴም የፀረ ክትባት አቋም የለኝም፡፡ ነገር ግን እንደህክምና ባለሙያ ለሰዎች የሚሠጥ ማንኛውም ነገር ለተቀባዮቹ መነገር አለበት የሚል ቀን ከቀን ከምሠራው ሙያ ጋራ የተያያዘ የሙያ ግብረገብ ስላለኝ ነው፡፡ እንደገናም ጥያቄው፣ ክትባቱ መኖሩና አለመኖሩ ሳይሆን፣ የሚሰጣቸው ወጣት ሴቶች ወይም ሴቶች ተነግሯቸዋል ወይ? ነው፡፡
ፀጉርዎ ለመድሃኒት መጠን መለኪያ
ሊሆን እንደሚችል ያውቃሉ ወይ?
ሕሙማን መድሓኒት ሲወስዱ፣ መድሐኒቱ በሰውነታቸው በበቂ መጠን ለመኖሩ ምርምራ ሲደረግ የነበረ ነገር ነው፡፡ ይህም በደም ምርመራ በተጨማሪም በሽንት ምርመራ በማድረግ ነበር የሚታወቀው፡፡
እንግዲሕ የመድሐኒት መጠን በሰውነተ ውስጥ በበቂ መጠን መኖሩ በአብዛኛው የሚደረገው የህክምና ጥናት ላይ የምርምር መድሀኒቶች በሚወስዱ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ሕሙማን በትክክል ለህክምና የተፈቀደላቸውን መድሐኒት ሳያቋርጡ መውሰዳቸውን ለማጣራት ወይም ለማረጋገጥም ይደረጋል፡፤
ከላይ ከተጠቀሱት ሁኔታዎች ውጩ በብዛት የሚደረገው ምርመራ፣ ሰዎች ለሥራ ሲቀጠሩ ያልተፈቀዱ ዕፆችን ተጠቃሚ መሆናቸውና አለመሆናቸውን ለማወቅ ነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ አልፎ አልፎ ደም ቢሰጥም በአብዛኛው የሽንት ምርመራ በማድረግ ነው፡፡
አሁን ግን ሽንት ምርመራው ቀርቶ ሌላ ዘዴ ብቅ ብሎ አልፎ አልፎም አንዳንድ ቦታዎች ላይ አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው፡፡ የሽንት ምርመራ ሲደረግ፣ ለምርምራ የተሠጠው ሽንት የተፈላጊው ሰው ሽንት ነው ወይስ የሌላ ሰው ነው የሚለውን ለመመለስ፣ ሽንት ሲሰጥ የሚደረግ ጥንቃቄ አለ፡፡ አሁን ግን ይህ አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም የዚህ አይነቱ ምርመራ ቀጥታ ከተመርማሪው ፀጉር መደረግ ይችላል፡፡ Liquidchromatography በተባለ ቴክኒክ የሚፈለጉት የመድሓኒት አይነቶች መጠን መለካት ይቻላል፡፡ ሰለዚህ ፀጉር ለጌጥና ለብርድ መከላከያ ከመሆን አልፎ ሌላ ቁም ነገር ተገኘበት ማለት ነው፡፡
ለፈገግታ ያህል፣ ሕገወጥ ዕፅ የሚጠቀሙ ሰዎችን ፀጉር የሚያሰተካክሉ (የሚቆርጡ) ሰዎች አደጋ ላይ ይሆኑ ይሆን?
ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ
Community health
education in Amharic